ሶስት ባሀለብቶች ሆቴላቸውና መኖሪያ ቤታቸው ለለይቶ ማቆያ እንዲያገለግል ወሰኑ

48

ማይጨው ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ ሶስት ባለሃብቶች ሆቴሎቻቸውና የመኖሪያ ቤታቸውን ለኮሮና መከላከል ስራ አንዲያገለግል ወሰኑ ።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ካልአዩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎችን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ከንክኪ ነፃ ሆነው እንዲቀመጡ ማድረግ አንዱ መከላከያ መንገድ ነው ።

በሽታው አዲስና ድንገተኛ ወረርሽኝ በመሆኑ ከሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ውጪ ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ቦታ አለመኖሩ የመከላከል ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል።

በዞኑ የሚንቀሳቀሱ ሶስት ባለሀብቶች ችግሩን በመገንዘብ ሆቴላቸውና መኖሪያ ቤታቸው ለዚህ አገልግሎት እንዲውል በፍቃደኝነት መሰጠታቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።


አቶ ሓዱሽ ረዳ የተባሉ ባለሀብት በማይጨው ከተማ የሚገኘውና ለምለም ተብሎ የሚጠራው 30 አልጋዎች ያሉት ሆቴል ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት እንዲውል ወስነዋል ።

በመኾኒ ከተማ 40 አልጋዎች ያለው የባላንስ ሆቴል ባለቤት አቶ ሀብታሙ  ፍቃዱ የተባሉ ባለሀብት ደግሞ ሆቴላቸው ለማቆያና ለማገገሚያ አገልግሎት እንዲውል በመወሰን ለህዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት በተግባር አሳይተዋል ።

ኑሮአቸውን በአሜሪካን አገር  ያደረጉት አቶ  መሳይ በላይ የተባሉ  የአካባቢው ተወላጅ  በመኮኒ ከተማ የሚገኝ  መኖሪያ ቤታቸው ለዚህ አገልግሎት እንዲውል ማስረከባቸውን ወይዘሮ ሙሉ ተናግረዋል።


ባለሀብቶች በተጨማሪም  የእጅ መታጠብያ ሳሙናና ሳኒታይዘር   የመሳሰሉ  ድጋፎች   ማድረጋቸውን ከኃላፊዋ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም