ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለገሱ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሥራ እንዲውል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለገሱ።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በታህሳስ ወር 2019 በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን አዳርሷል።

በዚህም እስካሁን ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከተከሰተበት መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 25 ዜጎች የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው ተረጋግጧል።

መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭት አሁን ካለበት ሊብስ እንደሚችል በመስጋት በፌደራልና በክልሎች ደረጃ የሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የአንድ ወር ደመወዛቸውን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሥራ እንዲውል መለገሳቸው ይታወቃል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮችም በዛሬው ዕለት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዝ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወስነዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ እና አራቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም