ቀጥታ፡

በተናጥል ጉዞ ኮሮናን ማሸነፍ አይቻልም--አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

መጋቢት 22/2012 (ኢዜአ) በተናጥል ጉዞ ኮሮናን (ኮቪድ-19) ማሸነፍ እንደማይቻል በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ አስታወቁ።

አምባሳደሩ በሽታውን በጋራ ለመከላከል ለአለም አቀፍ ማኅበረሰብ የትብብር ጥሪም አቅርበዋል።

በቅርቡ ከቻይና በየነ መረብ መረጃ ማዕከል ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት ሀገራት ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ ሀብታምም ሆነ ድሃ ፣ ደቡብም ሆነ ሰሜን በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

የቫይረሱ ስርጭት ድንበር የለሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትብብር ከመስራት ውጭ ሀገራት ሌላም ምንም አይነት አማራጭ የላቸውም ብለዋል አምባሳደሩ።

ችግሩ አለም አቀፋዊ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ለዛ ነው ችግሩን ለመመከት ዓለም አቀፍ ትብብር እና ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ አስፈላጊ በመሆኑ ለአለም ጤና ድርጅት አስፈላጊ ሀብትና የገንዘብ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮዽያንና የቻይናን ግንኙነት የቆየ መሆኑን ያወሱት አምባሳደሩ ኢትዮዽያ ቻይና አጋጥሟት በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላሳየችው ድጋፍና አጋርነት ልዩ እንደነበር ተናግረዋል።

በዚህም አሁን አፍሪካ ቫይረሱን ለመዋጋት እያደረገችው ላለው ጥረት ቻይና ዋነኛ አጋርነቷን እያሳየች እንደሆነ የጠቆሙት አምባሳደር ተሾመ፤ እየተደረገ ላለው የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ምሳጋቸውን አቅርበዋል።

በመሆኑም የቻይና አፍሪካ ትብብር ቫይረሱን ለመዋጋት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የፓን አፍሪካ ትብብርን የሚያጎላ እንደሆነም ገልጸዋል።

በገለልተኝነት እና በተናጥል ጥረት ችግሩን መቅረፍ ስለማይቻል አሁን ጊዜው ይበልጥ የተቀናጀ እና የተናበበ ዓለም አቀፍ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም