አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ከሰኔ 28 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ከሰኔ 28 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ከሰኔ 28 ቀን ጀምሮ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ውድድር ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተውጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ተተኪ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ ነው። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደቶች ውድድሮች እንደሚካሄዱም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው ዓመት የብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሶስት ጊዜ ያካሄደ ሲሆን አዲስ አበባ፣ ሆሳዕናና ጎንደር ውድድሩ የተካሄደባቸው ቦታዎች ናቸው። በአዲስ አበባ የሚካሄደው ውድድር የዘንድሮ ዓመት የክለቦች መዝጊያ ውድድር እንደሆነና በአጠቃላይ በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ተደምሮ የ2010 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ይሰጥ ነበር። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። የክለቦች ምስረታም በዚያው ወቅት የተጀመረ ሲሆን በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። ስፖርቱን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም ተመስርቷል።