ቤንዚን በህገ- ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የነበሩ የነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጆች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ቤንዚን በህገ- ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የነበሩ የነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጆች ተያዙ
አሶሳ፣ መጋቢት 20/2012 (ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ ከአስር በርሜል በላይ ቤንዚን በህገ- ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የነበሩ ሁለት የነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጆች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
ግለሰቦቹ የተያዙት ለነዋሪዎች ደህንነት ተብሎ በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካኝነት ትናንት ምሽት መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ ወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት ባለቤት ረዳት ኢንስፔክተር ደረጀ ኢታና ለኢዜአ ገልጸዋል።
በከተማው የተባበሩትና ኦይልሊቢያ ነዳጅ ማደያዎች ሥራ አስኪያጆች የሆኑት ግለሰቦቹ ቢንዚን ከማደያዎቹ ቀድተው በበርሜልና በጀሪካን ከፋፍለው በከተማው በተለያዩ ቦታዎች በማከማቸት በምሽት ለማጓጓዝ ሲሞክሩ ግብረ ኃይሉ ሊደርስቧቸው ችሏል።
ቤንዚኑን በአሶሳ ወረዳ አብርሐሞ ቀበሌ አድርገው ወደ ወረዳዎች በማሻገር በጥቁር ገበያ በሊትር እስከ 100 ብር ለመሸጥ ያዘጋጁት እንደነበርም ረዳት ኢንስፔክተሩ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የህገ-ወጥ ቤንዚን ተቀባዮችን ለመያዝም ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ግብረ ኃይሉ በተለይ ህዝብና መንግስት ፊታቸውን ወደ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ማዞራቸውን ተከትሎ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ግብረ ኃይሉ ከ20 ቀናት በፊት 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተዘረፉ ንብረቶችንና ከ50 በላይ የተደራጁ የዘረፋ ወንጀል ተጠርጣሪዎችን መያዙን በወቅቱ መዘገባችን ይታወቃል።