ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ስኬታማነት የበኩላችንን እናበረክታለን….የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ስኬታማነት የበኩላችንን እናበረክታለን….የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂዎች
ጎንደርሰኔ24/2010ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ስኬታማነት የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ሚና የጎላ በመሆኑ ለውጡን እንደሚደግፉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ ከእጩ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የስነ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ አማረ ሞላ እንዳለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የለውጥ እርምጃ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር እስከ ዳር ያነሳሳ ነው፡፡ “የነገ አገር ተረካቢ የሆንነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራቂዎች በለውጥ እርምጃው አዲስ ተስፋን ሰንቀናል” ያለው ተማሪው ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚቆሙ ተናግሯል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የለውጥ ጎዳና ግቡን የሚመታው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑን የጠቆመው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ሌላው እጩ ተመራቂ አበራ ታደሰ ነው፡፡ “ለውጡ በእኛ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ በመሆኑ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋችን አይለያቸውም” ብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አመራርነት በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በህዝቡ ውስጥ የፈጠሩት ሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት አስተሳሰቦች ያለልዩነት በህዝቡ ዘንድ ከፍትኛ ድጋፍ ያስገኘላቸው በመሆኑ አላማቸው እንዲሳካ ከጎናቸው ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። “ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን አክብሮትና ድጋፍ በየአካባቢው በተለያየ መንገድ መግለጹ ከፈጠረብኝ መነሳሳት ባለፈ በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ አድርጎኛል” ያለው ደግሞ በትምህርት አመራር በመጀሪያ ዲግሪ ለመመረቅ የተዘጋጀው ተማሪ ግዴሳ ግርማ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነትና የአጋርነት መገለጫ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ሙያ ሀገሩን የሚጠቅም ሥራ በኃላፊነት ሲያከናውን በመሆኑ እኔም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በቀሰምኩት እውቀትና ክህሎት አገሬን በማገልግል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ለውጥ እውን ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል። በዩኒቨርሲቲው ስነ ትምህርት ክፍል በመጀሪያ ዲግሪ ዘንድሮ የሚመረቀው ማቼስ በየነ በበኩሉ በምረቃ ዋዜማ ለውጥ ፈላጊና አራማጅ መሪ በአገሪቱ ወደ ስልጣን በመምጣቱ ውስጣዊ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል፡፡ “ሳይማር ያስተማረኝን ቤተሰብና ህዝብ የማገልገል ጽኑ ፍላጎት አለኝ” ያለው ተማሪው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ እርምጃ በአገሪቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያበሰረ በመሆኑ ለውጡን እንደሚደግፍ ገልጿል። እንደተማሪው ገለጻ በአዲስ አበባ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋናና ድጋፍ ለማቅረብ ሰልፍ በወጡ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ለውጡን የሚያጠናክር እንጂ የሚያደናቅፍ አይሆንም። ለተጎዱ ወገኖች ህዝቡና መንግሰት ላሳዩት ፈጣን ድጋፍ አድናቆት እንዳለውም ተናግሯል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ5ሺህ በላይ ተማሪዎች የፊታችን ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚያስመርቅ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡