ቀጥታ፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በድጋፍ አገኘ

ጎንደር፣  መጋቢት 20/2012 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ስድስት የሰው ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን በድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ በአከባቢው ቢከሰት ለህሙማን ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ 25 ሺህ አልጋዎች ማዘጋጀቱም ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ መሳሪያዎቹን በድጋፍ ያገኘው አቶ አይሸሹም ተካ ከተባሉ በውጪ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጅ ነው፡፡

የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎቹ ሆስፒታሉ እያዘጋጀ ባለው የማቆያ ማዕከል ሊመጡ የሚችሉ የቫይረሱ ተጋላጮችን ለመለየት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በህክምና ቀጠሮ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ህሙማንና አስታማሚዎች ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ልየታ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡

የመሳሪያዎቹ በድጋፍ መገኘትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ቅድመ ምርመራ ውጤታማ እንዲሆን የላቀ ሚና እንደሚኖረው ዶክተር አስራት አስረድተዋል።

በጎ አድራጊ ግለሰቡ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ተጨማሪ የህክምና ግብአቶችን ለማቅረብ ቃል መግባታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ዩኒቨርሲቲው ፀዳ፣ ማራኪ፣ ቴዎድሮስና ኢንጅነሪንግ ካምፓሶችን እንዲሁም የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ይገለገሉባቸው የነበሩ 25 ሺህ አልጋዎች ለተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያ እንዲሆኑ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የህንጻዎቹን ንጽህና ከማስጠበቅ ጀምሮ በቂ የመብራትና የውሃ አገልግሎት እንዲሟላላቸው እንዲሁም አልጋና ፍራሾችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውና 476 አልጋዎች ያሉትን ባለ አራት ፎቅ የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍል በመጪው ሳምንት ከተቋራጩ በመረከብ ለዚሁ አገልግሎት ለማዋል መታቀዱንም ዶክተር አስራት አስታውቀዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ ለመከላከል በየደረጃው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑም  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም