ቤተ ክርስቲያኗ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ያቋቋመችው ግብረ ሃይል ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ ክርስቲያኗ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ያቋቋመችው ግብረ ሃይል ስራ ጀመረ
መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ያቋቋመችው ተስፋ ልኡክ ግብረ ሃይል በስሩ አራት ንኡስ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀች ።
የቤተ ክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዶስ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን አስመልክቶ መጋቢት 11 ቀን 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ካህናት፣መምህራነ ወንጌልና የጤና ባለሙያዎች የተካተቱበት "ተስፋ ልኡክ"የተሰኘ ግብረ ሃይል ማቋቋሙ ይታወሳል።
ግብረ ሃይሉ ከተቋቋመበት ዕለት ጀምሮ የተለያዩ ቅድመ ተግባራትን ሲያከናውን የነበረ ሲሆን በስሩ አራት ንኡስ ኮሚቴዎችንም አቋቁሟል።
ኮሚቴዎቹም የትምህርት ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት፣የድጋፍ አሰባሳቢና ፋይናንስ፣ የቴክኒክ አደጋ ዝግጁነትና ትንበያ እንዲሁም የአህጉረ ስብከት ኮቪድ 19 ተስፋ ልኡክ ክትትል ንኡስ ግብረ ሃይሎች ናቸው።
ንኡስ ኮሚቴዎቹ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር የሚያስተሳስር ወጥ የሆነ አሰራር ተዘርግቶና ተግባርና ሃላፊነት ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውንም ግብረ ሃይሉ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት በሁሉም አህጉረ ስብከት፣ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ግብረ ሃይሉ በንኡሳን ኮሚቴዎቹ ተግባርና ሃላፊነት መሰረት ስራውን ጀምሯል።
በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ቤተ ክህነት መግቢያና መውጫ ላይ የኮቪድ 19 ምርመራ መጀመሩንም ግብረ ሃይሉ በመግለጫው ጠቅሷል።
በአዲስ አበባ በሁሉም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ለሚገኙ የቤተ እምነት አስተዳዳሪዎች የቫይረሱን ስርጭት፣መከላከልና የቤተ ክርስቲያኗን ቀጣይ አስተዋፅኦ በተመለከተ የማስተማሪያ ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም አሳውቋል።
የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ የሚመጡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ለመቀነስ እንዲቻል ህዝበ ክርስቲያኑ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በተቋቋመው ግብረ ሃይል በኩል የተቻለውን ሁሉ እንዲለግስ ጥሪ አቅርቧል።
በተለይም አቅመ ደካማ አረጋዊያንና በጎዳና ላይ ያሉ ዜጎች የበለጠ ተጎጂ ሊሆኑ ስለሚችሉ የበሽታ መከላከያ ቁሳቁሶች፣ምግብ፣ መጠጥና መሰል ድጋፎችን በማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል።
ህዝበ ክርስቲያኑም ይሁን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለበሽታው መከላከል ታስበው የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉና የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።