ባለፈው 24 ሰአት የኮሮና ቫይረስ ምልክት ያሳዩ 79 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፈው 24 ሰአት የኮሮና ቫይረስ ምልክት ያሳዩ 79 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተገለጸ
መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ)ባለፈው 24 ሰአት የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክት ያሳዩ 79 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።
ባለፈው 24 ሰዓት ውስጥ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክት ያሳዩ 79 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ እንደተረገላቸውና ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን ኢኒስቲትዩቱ ኮቪድ -19 አስመልክቶ ባወጣው ዕለታዊ መግለጫ አስታውቋል።
ለ14 ቀናት ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው 2 ሺህ 90 ሰዎች ክትትላቸው እንዲረቋጥ መደረጉንም ገልጿል።
ከመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት ስድስት ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ ሀገር የሚመጣ መንገደኛ በተመረጡ ሆቴሎች ውስጥ በራሱ ወጪ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆዩ የተወሰነ መሆኑ ይታወቃል።
በውሳኔው መሰረት እስካሁን 636 መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና በተመረጡ 10 ሆቴሎች ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ የኢንስቲትዩቱ መግለጫ ያሳያል።
መንገደኞቹ ባሉባቸው ሁሉም ሆቴሎች የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተመልክቷል።
የውጭ አገራት መንገደኞች የለይቶ ማቆየት ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 873 ሰዎች በቤታቸው ሆነው በስልክ ለ14 ቀን በጤና ባለሙያዎች የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 16 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው በላቦራቶሪ ምርመራ መረጋገጡ ቀደም ብለው በተሰጡ መግለጫዎች ማሳወቁን ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።
አስራ ስድስት (16) ታማሚዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን 14 ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስታውቋል።
የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸውና የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ከሚገኙ ታማሚዎች ውስጥ አንድ ታማሚ በድጋሚ በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት ተጨማሪ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚቆዩ ተገልጿል።
አሁን ባለው ሁኔታ 13 ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንደሚገኙና ከነዚህ ውስጥ ጽኑ ታማሚ እንደሌለም ተመልክቷል።