በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሰዎች መካከል አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ አገግሟል ... የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሰዎች መካከል አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ አገግሟል ... የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት 16 ሰዎች መካከል አንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ ማገገሙን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ያገገመው ሰው ለጥንቃቄ ሲባል ለአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሚቆይ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ እስካሁን 797 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርምራ እንደተደረገላቸውና ከነዚህ ውስጥ 16 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ከተያዙት 16 ሰዎች አንዱ ሰው ሙሉ ለሙሉ ማገገሙን የኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የታማሚዎች መረጃ በሚያሳየው ሰሌዳ ላይ ተመልክቷል።
አንድ ታማሚ ከኮሮናቫይረስ በሽታ ሙሉ ለሙሉ አገገመ የሚባለው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ምንም አይነት ምልክት ሳይኖረው ሲቆይ እና በሚደረግለት ሁለት ተከታታይ የላቦራቶሪ ምርመራ ነጻ ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቋል።
ምንም እንኳ ግለሰቡ/ቧ ነጻ ቢሆንም ለጥንቃቄ ሲባል በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለ14 ቀናት የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሚቆይም ገልጿል።
በዚሁ መሰረት ሙሉ ለሙሉ ያገገመው ሰው ለ14 ቀናት የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይቆያል ተብሏል።