ቀጥታ፡

በድሬዳዋ በለይቶ ማቆያ የነበሩ ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ሆኑ

ድሬዳዋ/ኢዜአ/ መጋቢት 18/2012  ከጅቡቲ ከተመለሱ 814 ኢትዮጵያዊያን መካከል በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ የነበሩ 3 ሰዎች ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አዋሳኝ ከሆነው የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ጋር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከጅቡቲ ወደ ሲቲ ዞን ከገቡ 814 ኢትዮጵያውያን መካከል ሶስቱ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው የደም ናሙናቸው ወደ አዲስ አበባ ለምርመራ ተልኮ ነበር ።

ለሁለት ሳምንታት ከድሬዳዋ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው የጉምሩክ ኮሚሽን አዲስ ህንፃ ተለይተው ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩት ሶስቱ ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ትውልድ ስፍራቸው እንዲሔዱ ተደርጓል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አስተዳደሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ለማገዝ ባለሃብቶች፣ግለሰቦችና ተቋማት የመከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል ።

ዳዊት ለአረጋውያን የአዛውንቶች መረጃ ተቋም ለ9 መቶ አቅመ ደካሞች የንጽህና መጠበቂያ የሰጠ ሲሆን ሸሙ ፋብሪካ በበኩሉ  የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 200 ካርቶን ደረቅና 200 ባለ 5 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ድጋፍ አድርጓል፡፡  

በግለሰብ ደረጃ ዶክተር ፈቲህ መሐመድ 40 ሺህ ብር የሚያወጣ የሰውነት ሙቀት መመርመሪያ መሳሪያ ለድሬዳዋ አስተዳደር አስረክበዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ እየተደረገ ለሚገኘው ድጋፍ አመስግነው ሌሎችም ይህንኑ በመከተል ችግሩን በጋራ ለመከላከል እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ሀገር አቀፉን የኮሮና ቫይረስ የመከላከል አቅጣጫ ተከትሎ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም