ቄለም ወለጋ ዞን ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቄለም ወለጋ ዞን ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች ነው
መጋቢት 19/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የቄለም ወለጋ ዞን ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች እንደሆነ የክልሉ ፕሬዚዳን አቶ ሽመልስ እብዲሳ ገለጹ።
የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ እንደሚጀምርም ተናግረዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳና እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ትናንት በቄለም ወለጋ ዞን ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በሰላምና ደህንነት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በቄለም ወለጋ ዞን አሁንም ችግሮች የሚታዩ ቢሆንም አንጻራዊ ሰላም መምጣቱንና ሰዎች ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የቄለም ወለጋ ዞን ላለፈው አንድ ዓመት የግጭት ማዕከል እንደነበረችና በዚህም ምክንያት ብዙ ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸው እንዳለፈ አቶ ሽመልስ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።
''የክልሉ መንግስት ሰላምን ለማስከበር በወሰዳቸው እርምጃዎች ቄለም ወለጋ ዞን ወደ ሰላምና መረጋጋት ከመመለስ አኳያ ተጨባጭ ውጤቶች መጥተዋል'' ብለዋል።
በዞኑ ከመጣው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት በኋላ የተለያየ የልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደስራ ለመግባት ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ግንባታ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን ያካተቱ እንደሆኑና የዞኑን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው አቶ ሽመልስ የገለጹት።
በተጨማሪም በቄለም ወለጋ ዞን ባለው ችግር የተነሳ ተዘግቶ የነበረው የደምቢዶሎ አየር ማረፊያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
አየር ማረሚፊያው ስራ መጀመሩ በዞኑ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚያቀላጥፍ ተናግረዋል።
በውይይቱ ወቅት የቄለም ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ከሰላምና ልማት ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል መንግስት መፍታት ይገባዋል ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡትም ምላሽ የክልሉ መንግስት በዞኑ የህግ የበላይነትና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እንዲመጣ አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዞኑ የተቋረጠው የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መፍትሄ የሚሰጠው መሆኑንም አመልክተዋል።