ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት ቀናት ውስጥ ለ39 የአፍሪካ አገሮች የህክምና ቁሳቁሶችን አቀረበ

አዲስ አበባ መጋቢት 18 / 2012 ዓ.ም. (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት ቀናት ውስጥ ለ39 የአፍሪካ አገሮች ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መከላከል የሚውል የህክምና ቁሳቁሶችን አቀረበ።

ዓለም በኮሮናቫይረስ ቀውስ ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገሮች አጋርነቷን እያሳየች እንደሆነም ተገልጿል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥረት ከአሊባባ መስራች ጃክ ማ ለአፍሪካ አገሮች የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያዳረሰ ይገኛል።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በጃክ ማ የተደረገውን ድጋፍ ኢትዮጵያ በፍጥነት ለአፍሪካ አገሮች እያዳረሰች ነው።

የመመርመሪያ ኪት፣ የአፍ መሸፈኛ ማስክ፣ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳት ለአገሮቹ እንዲደርስ መደረጉን አየር መንገዱ ገልጿል።

''የአፍሪካ አገሮችን በሰላምና በችግር ወቅት በመድረስ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ይህንን ታሪኳን በመድገም በዚህ የቀውስ ጊዜ አጋርነቷን እያሳየች ነው'' ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ''በዚህ የቀውስ ወቅት የአፍሪካን ህዝቦች ለማገልገል የሚያስችል እድል የፈጠሩልንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና ጃክ ማ'ን ማመስገን እንወዳለን'' ብለዋል።

''በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መመሪያ ሰጪነትና በጃክ ማ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም በአጋሮቻችን ትብብር ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚያገለግሉ ቁሳቁችን ለ39 የአፍሪካ አገሮች በአምስት ቀናት ውስጥ በማዳረሳችን ደስተኞች ነን'' ሲሉ ገልጸዋል።

የመከላከያ የህክምና ቁሳቁሶቹ በአብዛኛው ለአገሮቹ የተሰራጩት በእቃ ጫኝ አውሮፕላኖች አማካኝነት ነው።

ስርጭቱ በቀጣይ ቀናት የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።

የአሊባባ መስራች እና ባለቤት ጃክ ማ የአፍሪካ አገሮች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል ድጋፍ ለማድረግና ለማሰራጨት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር በደረሱት መግባባት ኢንሽዬቲቩን አቋቁመዋል።

በዚህ ኢንሼቲቭ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቫይረሱን ለመመርመር የሚያስችሉ መሳሪያዎች፣ 6 ሚሊዮን የአፍ መሸፈኛ ማስኮችን ጨምሮ 60 ሺህ የሚጠጉ ከቫይረሱ ጋር ንክኪ እንዳይኖር የሚከላከሉ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳት ለአፍሪካ አገሮች ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም