የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2012(ኢዜአ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና የሚያስከትለውንም ማህበራዊ ቀውስ ለመቀነስ የሚያስችል የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ይፋ አደረገ።
በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል አገራት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም የቫይረሱን መስፋፋት ለመቀነስ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለተግባራዊነቱ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በዛሬው እለትም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መከላከል ታሳቢ ያደረገ የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ይፋ ሆኗል።
ፕሮቶኮሉን ይፋ ያደረጉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ማለት በአሰሪውና በሰራተኛው ዘንድ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንዲሁም የአሰራር ሂደቶች የሚያስፈፅም ስምምነት ነው።
ፕሮቶኮሉ መንግስት፣ አሰሪዎችና ሰራተኞችን የሚወክሉ አካላት በተገኙበት የሶስትዮሽ ስምምነት ተደርጎበት ይፋ ተደርጓል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የስራ ቦታ ፕሮቶኮሉ ዋና አላማ የሰራተኞችንና የስራ አመራሩን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ነው።
በመሆኑም ሰራተኞችና አሰሪዎች የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል የጋራ ጥንቃቄና መከላከል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በፕሮቶኮሉ መሰረትም የወረርሽኙ ስርጭት እንዳይባባስ አሰሪዎች የሰራተኞች የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዲያሟሉና አካላዊ ጥግግት እንዳይኖር ማድረግ አለባቸው።
በሚቀጥሉት 12 ወራት ለሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ፣ የተለያዩ አበሎችና እንደ ደመወዝ የማይቆጠሩ ክፍያዎች ባይኖር የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የሰራተኞችን ጥቅማጥቅም የሚያሳጡ ውሳኔዎች ድርጅቶች ከሰራተኞች ጋር በመመካከር ሊተገብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል።
መመሪያው በአሰሪውና ሰራተኛው መካከል መተሳሰብንና ድርጅቶች ላይ የሚመጣውን ቀውስ ከመታደግና የሰራተኛውም ጤንነት ለመጠበቅ አጋዥ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሪሽን ፕሪዘዳንት አቶ ታደለ ይመር ገልጸዋል።