አይ ኦ ኤም ባለፉት 2 ዓመታት ከ2 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን መልሶ ማቋቋሙን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
አይ ኦ ኤም ባለፉት 2 ዓመታት ከ2 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን መልሶ ማቋቋሙን ገለፀ
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ባለፉት በፈረንጆቹ ሁለት ዓመታት ከ2 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ማቋቋሙን አስታወቀ።
በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ፕሮግራም አስተባባሪ ሳራ ባሻ ለኢዜአ እንዳሉት ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመት ተመላሾችን መልሶ እያቋቋመ ያለው ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ነው።
በዚህም ለስደት ተመላሾች ከኢኮኖሚና ማህበራዊ ድጋፍ በተጨማሪ የስነልቦና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ነው የተናገሩት።
የትምህርት፣ ጤና እና መሰል አገልግሎቶችን ማመቻቸት ድርጅቱ በማህበራዊ መልሶ ማቋቋም ላይ የሚሰራባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ድርጅቱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2017 እስከ ተጠናቀቀው 2019 ድረስ 2 ሺህ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋሙንም አስታውቀዋል።
በተለይ በህብረተሰቡ የኢኮኖሚ ችግሮች ላይ አተኩረው የሚሰሩ መርሃ ግብሮች እንዳሉ ጠቁመው የስደት ተጋላጮችን የተመለከተ መርሃ ግብር ተቀርፆ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በጥናት በተለዩና ከስደት የተመለሱ በርካታ ዜጎች በሚኖሩባቸው ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ላይ ከማህበረሰቡና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመሆን መርሃግብሮቹ እንደሚተገበሩ አስረድተዋል።
"በድርጅቱ ድጋፍ እያገኙ ያሉት ዜጎች ቁጥር ካለው ፍላጎት አንጻር ትንሽ ነው" ያሉት አስተባባሪዋ፣ አሁንም በሥራ ፈጠራ፣ ህጋዊ የጎዞ መንገድን በማመቻቸትና ግንዛቤን በመፍጠር በኩል ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
መንግስትም በስደት ተመላሾች ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎች ዘለቄታ እንዲኖራቸው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዜጎች ከህገ ወጥ ይልቅ ህጋዊ መንገድን ተከትለው እንዲሄዱ በማድረግ የስደት ተመላሾችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከወኑ መሆናቸውን አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ታዬ በተያዘው በጀት ዓመት ከ14 ሺህ በላይ ዜጎችን ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ወዳደረጉ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ጆርዳን እና ኳታር በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ መደረጉን ለእዚህ በማሳያነት ገልጸዋል።
አቶ ደረጀ እንዳሉት ከ800 በላይ ኤጀንሲዎችም በአገሪቱ ፍቃድ አግኝተውና ተመዝግበው በመስራት ላይ ናቸው።
ዜጎች ህጋዊውን መስመር ተከተለው እንዲሄዱ ሚኒስቴሩ እየሰራ ካለው የግንዛቤ ሥራ በተጨማሪ ከኤጀንሲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚኒስቴሩ የሰለጠኑ ሠራተኞችን ወደ ውጪ አገራት ለመላክ ከኢምባሲዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማትና ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ከስደት የተመለሱ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ከማደረግ ባለፈ በተዋረድ ካሉ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከ2009 እስከ 2011ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከ100 ሺህ በላይ ተመላሾች ወደ ሥራ እንዲሰማሩም ድጋፍ ተደርጓል።
የፌዴራል ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 2 ሺህ የሚጠጉ ከስደት ተመላሾች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጿል።
የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ እንዳሉት ኤጀንሲው በሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት ከሰጣቸው ዜጎች ውስጥ ከስደት ተመላሾች ይገኙበታል።
ኤጀንሲው ተጎጂ ስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ ያለውን ቡድን በሰብሳቢነት እየመራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ2012 የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ለ10 ሺህ ስደት ተመላሾች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በማደራጀት የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን አንስተዋል።
ይሁንና አፈጻጸሙ 1 ሺህ 919 ወይም የዕቅዱ 20 በመቶ አካባቢ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በፌደራል ደረጃ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻግር ወንጀልን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ስር ያሉ ተቋማት ስራውን በኃላፊነት አለመስራታቸውና እኩል ተሳትፎ አለማድረግ ለአፈጻጸሙ ማነስ በመንስኤነት ጠቅሰዋል።
ስደተኞቹ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እንደተደረገም ወይዘሮ አቦዘነች አንስተዋል።