የአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል ያወጣው መመሪያ ሳይሸራረፍ መተግበር አለበት...ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተመስገን - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ኮሮናን ለመከላከል ያወጣው መመሪያ ሳይሸራረፍ መተግበር አለበት...ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተመስገን

ባህርዳር መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) የአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመከላከል ያወጣውን መመሪያ እስከ ታችኛው የአስተዳድር መዋቅር በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
በክልሉ የተቋቋመው የኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ሴክሬታሪያት ቡድን ከግብረ ሃይልና ከኮማንድ ፖስት አመራሮች ጋር ሊያጋጥሙ በሚችሉ ችግሮች ዙሪያ ምክክር አድርጓል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የኮሮና ቫይረስን አስከፊነት በመገንዘብ አደጋውን ለመቀነስ በሚያደርጉት ጥረት የሴክሬታሪያቱን እገዛ ሊጠቀሙበት ይገባል።
"የክልሉ መንግስት ያወጣውን መመሪያ እስከ ታች በማውረድ ህብረተሰቡ ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ በማድረግ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መተግበር አለበት" ብለዋል።
አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስን መከላከል ግብረ ሃይልና የኮማንድ ፖስት በማቋቋም ወደ ስራ ቢገባም ስለበሽታው አስከፊነት፣ መከላከያ መንገዶችና የህክምና ሁኔታውን ለህብረተሰቡ በማስረጽ በኩል ውሱንነት ተስተውሏል።
"በመናኸሪያ፣ በገበያ ቦታዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚስተዋለው መተራመስ የሰራነው ስራ መለኪያ ማሳያ በመሆኑ በቀጣይ በችግሩ ልክ ተገንዝቦ መረባረብ ይገባል"ብለዋል።
በተለይም እስከታች ድረስ ያለው አመራር ህብረተሰቡን በማስተማር፣ በቁሳቁስ አቅርቦት፣ በህግ ማስከበርና ሌሎች ተግባራት ትኩረት በመስጠት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የኮቪድ-19 መከላከልና መቆጣጠር ሴክሬታርያት ሰብሳቢ ዶክተር አንዳርጌ ታዬ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳሳዩት በልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ኮረና ከተከሰተ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በሞትም ሆነ በበሽታው ስርጭት ምንም ለውጥ አልታየም ነበር።
ከወር በኋላ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ የሚሞተውን ሰው በእጥፍ በማሳደግ 1200 ከመድረሱም በላይ በኮረና በሽታ የተያዘውን ሰው ቁጥር ከ85ሺህ በላይ አድርሶታል።
በክልሉ ከተቋቋመው ግብረ ሃይልና ኮማንድ ፖስት ጋር በመተባበር ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስና ከተቻለም ለመግታት በጋራ ሌት ከቀን ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
"በዓለም ላይ ያለውን ተሞክሮ በመገንዘብ ነገ ከነገ ወዲያ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ለመግታት፣ ለመቋቋምና ከተከሰተም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት መስጠት አለባቸው" ብለዋል።
የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እንዳሉት ሰሞኑን ከዩኒቨርሲቲዎች መዘጋትና ከጸበል ቦታዎች ህዝቡ ወደ ቤተሰቡ ከመንቀሳቀሱ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ታይቷል።
ክልሉ ያወጣውን መመሪያ በግማሽ ቀንሰው መጫን እንዳለባቸው ሲነገራቸው ተሳፋሪውም ሆነ አሽከርካሪዎች መታዘዝ ባለመቻላቸው የጸጥታ ሃይል በመመደብ ህግ የማስከበር ስራ ለማከናወን መታሰቡንም ተናግረዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት ህብረተሰቡ በከተማዋ የወጣውን መመሪያ ከመተግበር ይልቅ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።
የከተማ አስተዳደሩ 10 ሚሊየን ብር በከንቲባ ኮሚቴው በመመደብ ለሸማቾች ማህበር በመደገፍ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ቢሞከርም የፋይናንስ ስርዓቱ ክፍተት ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በቫይረሱ እንደተያዙ ተጠርጥረው ክትትል ሲደረግላቸው ከቆዩት 12 ሰዎች መካከል 11ዱ ነጻ መሆናቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ቀሪው አንድ ሰው የምርመራ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ተመልክቷል።