የግል ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማህበር ለኮሮና መከላከያ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የግል ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማህበር ለኮሮና መከላከያ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማህበር መንግስት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የጀመረውን ንቅናቄ ለማገዝ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።
የጤና ትምህርት ክፍል ሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች በሙያቸው ማህበረሰቡን የሚያገለግሉበት ዕድል እንዲፈጠር ለትምህርት ተቋማቱ ውሳኔው ተላልፏል።
የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሞያ ተቋማት ማኅበር ስራ አመራር ቦርድ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ጸጋዬን ጨምሮ የቦርድ አባላቱ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ማኅበሩ የወቅቱን ዓለማቀፋዊ ክስተት ተከትሎ መንግስት ላቀረበው አገራዊ ጥሪ ምላሽ ማኅበሩ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ማኅበሩ ባሉት 118 አባል የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በቅድሚያ ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲከላከሉ፣ ቀጥሎም በኦንላይን ከሚወስዱት ትምህርት ጐን ለጎን የማህበረሰብ በጎፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ወስኗል።
ተማሪዎች ማህበረሰቡ በሸትውን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን፤ በተለይም የጤና ትምህርት ክፍል ሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች በሙያቸው ማህበረሰቡን የሚያገለግሉበት ዕድል እንዲፈጠር ለትምህርት ተቋማቱ ውሳኔው ተላልፏል።
ይህንም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በጎፈቃደኛ ተማሪዎችን በማሰባሰብ የሚጠበቅባቸውን ማህበራዊ ሃላፊነት እንዲወጡ ይደረጋል ተብሏል።
የማኅበሩ አባል ተቋማትም ሆኑ ሌሎች የግል ትምህርት ተቋማት ከሰው ሃይል ማህበረሰባዊ ግልጋሎታቸው በተጨማሪ የቁሳቁሱስና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከሰው ሃይል ማህበረሰብ አገልገሎት በተጨማሪም ማኅበሩ ከየተቋማቱ በየዓመቱ የሚያሰባስበውን 590 ሺህ ብር በሙሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የጸረ ኮረና ቫይረስ ንቅናቄ እንዲሰጥ ወስኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማኅበሩ ሌላው ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህደፋሴ ግደብ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይቴክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴም አገር ችግር ሲገጥማት የተማረው ህብረተሰብ ክፍል ቀዳሚ አስተዋጽኦ ማድርግ እንዳለበት ገልጸው፤ በዚህም "የተማረው አካል መፈተኛው አሁን ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ2 ሸህ በላይ ካምፓሶች ያላቸው 218 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዳሉ ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል 69 የሚሆኑት በተለያዩ የጤና መርሃ ግብር ላይ ተሰማርተዋል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ለተደቀነው ስጋት የጤና ተማሪዎች ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።