የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዦች ቁጥር 30 በመቶ ቀንሷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዦች ቁጥር 30 በመቶ ቀንሷል
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዦች ቁጥር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በ30 በመቶ መቀነሱን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የኮሮናቫይረስ ስርጭት በዓለም የአቬይሽን ኢንደስትሪው ላይ ከባድ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የኢትዮያ አየር መንገድ የዚህ ዓለም አቀፍ ዘርፍ ዋነኛ አካል በመሆኑ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 190 ሚለዮን ዶላር ኪሰራ አጋጥሞታል።
ቫይሩሱ መከሰቱን ተከትሎ የአየር መንገዱ ተጓዞች ቁጥርም አሁን ላይ 30 በመቶ መቀነሱን ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፉ የትራንፖርት ባለሥልጣን ሪፖርት በረራዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ የአፍሪካ አየር መንገዶች 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟቸዋል ብሏል።
ከባለፈው የፈረንጀች ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየካቲትና መጋቢት ወራት የተመዘገበው የጉዞ ምዝገባዎች 20 በመቶ ላይ እንዲንጠለጠል አድርጎታል።
በቫይረሱ ምክንያት የተሰረዙ የጉዞ ቲኬቶችም ብዛት ከአጠቃላዩ የጉዞ ምዝገባ 75 በመቶ ይሸፍናል ይላል የሮይተስ ዘገባ።
በአንጻሩ በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ ያለውን የሰው ኃይልና ኃብት በጭነት መጓጓዝ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በተለይም አየር መንገዱ ያሉትን 10 ከፍተኛ ጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በመጠቀም በዓለም ደረጃ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ ሁለትና ሶስት ወራት ከዚህ የከፉ ችግሮች ሊገጥሙና በኢንደስትሪው ላይ ከፍተኛ አደጋ አንደሚጥል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎም ዓለም አቀፉ የትራንፖርት ባለሥልጣን መንግሥታት አየር መንገዳቸውን እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረቡን ሮይተርስ ዘግቧል።