ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና ሱዳን አዋሳኝ ዞኖች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ውይይት ተካሄደ

መተማ ሰኔ 23/2010 በኢትዮጵያ ምዕራብ ጎንደርና በሱዳን አዋሳኝ ዞኖች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ውይይት ተካሄደ፡፡ በሱዳን ገላባት በተካሄደው በዚሁ ውይይት ከሱዳን በኩል የባሶንዳ፣ የዶካ፣ ቡሬሻና ዲንድር አስተዳደር ዞን አመራሮች ከምዕራብ ጎንደር ዞን እና ከአጎራባች የዞኑ ወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ በውይይቱም ህገ-ወጥነትን መከላከል፣ የጋራ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን፣ በባህልና በንግድ ማስተሳሰር በሚመቻልበት አግባብ አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በሱዳን በኩል የአራቱ አዋሳኝ ዞኖች አስተባባሪ ጀኔራል ሙሃመድ ሙሳ እንደተናገሩት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የዘለቀና በአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። ይህንኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የልማትም ሆነ የፀጥታ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የተሻለ መቀራረብና ጉርብትና ፈጥረው በጋራ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም በበኩላቸው " የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራና ህዝብ ለህዝብ የተሳሰረ ነው፤ ይህንን ለማስቀጠል በአዋሳኝ አካባቢ ያለን የአስተዳደር አካላት ግንኘነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ኃላፊት አለብ"ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ትስስር ጉዳይ በአዋሳኝ ባሉ አመራር ግንኙነት የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተልዕኳቸው ከዞንና ወረዳ ግንኙነት አልፎ ሀገራዊ አንድምታ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ በተያዘው ዓመተ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ በአርሶ አደር ደረጃ አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው ይህነኑ ችግር የሚፈታ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ "ኮሚቴው ኩታ ገጠምን መሰረት ያደረገ በሁለቱም አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው" ብለዋል፡፡ ኮሚቴው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በሁለቱም በኩል አዲስ የእርሻ ቦታ መስፋፋት እንዳይኖር፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የሰዎች ዝውውር መከላከልና ድንበር አካባቢ የታጠቀ ኃይል እንዳይኖር ማድረግ ይገኙበታል። እንዲሁም በሁለቱም በኩል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች እንዲመለሱ ማድረግ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን ማስመለስ፣ የታሰሩም እንዲፈቱ በማድረግ ለጋራ ጥቅም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን የመከላከል ስራዎች ይከናወናሉ። " በየዓመቱ እርሻ በመጣ ቁጥር ድንበር አልፎ የማረስ ሁኔታ በሁለቱም በኩል ስለሚፈጠር በዚህ ጉዳይ ተገናኝተን ጥሩ ስምምነት ላይ ደርሰናል " ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ በሱዳን የዲንድር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱላዚም አደም በበኩላቸው "አሁን ያለውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ድንበር አካባቢ ያለን አመራሮች በየጊዜው በመወያየት ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ አለመግባባቶችን መፍታት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡ በውይይቱ የተደረሰባቸው ስምምነቶች ህዝቡ የሚፈልጋቸውና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደንኤል ውበት ናቸው፡፡ ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱም የአስተዳደር አካላት ስጦታ ተለዋውጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም