ቀጥታ፡

ለተጠናከረ የኮሮና ቫይረስ መከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጤና ባለሙያዎች ገለጹ

ሀረር፣መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በሐረሪ ክልል የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

መምህራኑና የጤና ባለሙያዎቹ በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በከተማው በተለያዩ አደባባዮች ላይ ህብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤ የመስጠት ስራ አከናውነዋል።

የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ ጤና መምህር ሙመድ ዩያ እንደተናገሩት በክልሉ ቫይረሱን ከመከላከል አኳያ በማህበረሰቡ ዘንድ ከመቀራረብና ከመጠጋጋት እንዲሁም ከእጅ ንጽህና ጋር በተያያዘ መዘናጋት ይታያል።

"ይህንን በመረዳትም ለህብረተሰቡ ቫይረሱ የሚተላለፍበትን መንገድና መከላከል የሚቻልበትን ሁኔታ በተግባር፣በቃልና በሌሎች መንገዶች ግንዛቤ ለመፍጠር በየአደባባዩ እያስተማርን እንገኛለን" ብለዋል።

"ይህም የክልሉ መንግስት ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል እያከናወነ የሚገኘውን ጥረት ይበልጥ ለማጠናከር ይረዳል" ብለዋል።

"በሽታን አስቀድሞ ከመከላከል አኳያ የጤና ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ሚና ማበርከት ይገባናል" ያሉት ደግሞ የጤና ባለሙያና የኮሌጁ የህክምና መምህር ዶክተር ከድር ተጂ ናቸው።

"ለዚህም በተለይ ከመራራቅና ከንጽህና ጋር በተያያዘ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተጣለብንን ሃላፊነት ባግባቡ ለመወጣት እንሰራለን"ብለዋል።

በቀጣይም በህብረተሰቡ ላይ የሚታየውን መዘናጋት ለማቃለል በድሬዳዋና ጅግጅጋ ከተሞች ላይ ተመሳሳይ ስራዎችን በማከናወን መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

"የክልሉ ማህበረሰብ አብሮ የመኖር ባህልና ሁነቶችን በጋራ የማድረግ የቆየ እሴት ያለው ነው" ያሉት በሐረማያ ዩነቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ያደታ ደሴ ይህ ቫይረሱ በቀላሉ እንዲስፋፋ እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቫይረሱን ለመከላከልም በሆስፒታልና በኮሌጁ ከሚያከናውኑት ስራ በተጨማሪ ህዝብ በተሰባሰበበት ስፍራ በመገኘት የማሰተማሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ህዝቡ ጋር ወርደው በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙሪያ የሚሰጡት ትምህርት እሱን ጨምሮ የአካባቢውን ወጣቶች ያነቃ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ዲኖ ኢብራሒም ነው።

ያላቸውን እውቀትና ሙያዊ ኃላፊነት ተገንዝበው ህዝቡን ለማስተማር እየተንቀሳቀሱ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ይሄን መልካም ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

በከተማው በተለያዩ አደባባዮች ትላንት በተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ላይ ከ60 የሚበልጡ የህክምና መምህራንና የጤና ባለሞሙያዎች ተገኝተው በቃልና በምልክት የተደገፈ ትምህርት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም