በሞጆ ደረቅ ወደብ ዘመናዊ የኮንቴይነር ማራገፊያና የተሽከርካሪ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሞጆ ደረቅ ወደብ ዘመናዊ የኮንቴይነር ማራገፊያና የተሽከርካሪ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ተመረቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2010 የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሞጆ ደረቅ ወደብ የዘረጋቸውን ዘመናዊ የኮንቴይነር ማንቀሳቀሻና የበር ተሽከርካሪዎች መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ አስመረቀ። በተመሳሳይ ድርጅቱ በአዲስ የተተከለውን የኮንቴኔር ማንሻና ማውረጃ ቴክኖሎጂ ለማንቀሳቀስ ያሰለጠናቸውን 25 ተመራቂዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል። የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሚዴቅሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የሞጆ ደረቅ ወደብ አገልግሎቱን ለማዘመን በርካታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው። ከዚህም መካከል ወደቡን ከአዲስ አበባ-ደዋሌ ምድር ባቡር የሚያገናኝ የ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የባቡር ሃዲድ ተዘርግቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወራትን አስቆጥሯል። ወደቡ ኮንቴይነርን ለማመላለስ የባቡር ትራንስፖርትን መጠቀም መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ኮንቴይነሮችን ለማስተናገድ ከዚህ በፊት ከሚጠቀምበት የተንቀሳቃሽ የኮንቴይነር ማንቀሳቀሻ ወይም አር ኤስ ሪጅስታከር በሚባለው መሳሪያ ማስተናገድ አስቸጋሪ ነው። ስለሆነም ከዚህ በፊት በሰዓት በአማካይ ከ20 እስከ 25 ኮንቴይነሮችን ማስተናገድ ከሚቻልበት ተንቀሳቃሽ የኮንቴይነር ማንቀሳቀሻ በሰዓት 40 ኮንቴይነሮችን ከባቡር ላይ መጫንና ማውረድ የሚያስችል የአር ኤም ጂ ቴክኖሎጂ ወይም በአንድ ቦታ ተተክሎ ኮንቴይነሮችን አንቀሳቃሽ መሳሪያ ስራ ጀምሯል። ቴክኖሎጂው ወደቡ ከሚሰጠው አገልግሎት ፍጥነትና ከገንዘብ ወጪ አኳያ አዋጭ ነው ያሉት አቶ ደረጀ፤ የወደቡን ምርታማነትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደፊት የሚያራምድ እንደሆነ አብራርተዋል። መሳሪያውን የሚያንቀሳቅሱ ከ40 በላይ ባለሙያዎች እየሰለጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ዛሬ 25 ባለሙያዎች ተመርቀዋል። በሌላ በኩል ደረቅ ወደቡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ በር ላይ የተቀናጀ መረጃ ስርዓት ያለው የተሽከርካሪ መቆጣጠሪያ ገንብቷል። ተቋሙ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ተሳቢዎችን ለማስተናገድ ከዚህ በፊት የወረቀት ወይም ማኑዋል አሰራር ሲከተል እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም ተሳቢ የያዙ ደንበኞችን ማስገባት፣ መፈተሽና አስተናግዶ ማስወጣት ከፍተኛ የጊዜ ብክነትና የመረጃ ክፍተቶች ነበሩበት። ስለሆንም ተገልጋዩ በቢሮ እየተመላለሰ የሚወስድበትን ጊዜ በአንድ መስኮት አገልግሎት ማስተናገድ ስለሚቻል፤ የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂው ጊዜን ያሳጠረ፣ የመረጃ ስርዓቱንም ደህንነቱ የተጠበቀ አድርጎታል ብለዋል። በ2001 የተመሰረተው የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ሲመሰረት ከነበረበት ስፋቱ 2 ነጥብ 5 ሄክታር ወደ 144 ሄክታር፣ ከሁለት መጋዘን ወደ አራት መጋዘን፣ ኮንቴኔር የመያዝ አቅሙ ከ950 ወደ 14 ሺህ 900፣ ወደ ጅቡቲ የሚልካቸው ኮንቴይነሮች ብዛት ከ120 ሺህ ወደ 534 ሺህ እምርታ ማሳየቱ ተመልክቷል።