በምስራቅ ጎጃም ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ2 ተማሪዎች ህይወት አለፈ

171

ደብረ ማርቆስ መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ይዞ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ በመገልበጡ ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ በ22ቱ ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከል ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው በደጀን ወረዳ ጢቅ የትኖራ ቀበሌ ዛሬ ሌሊት 8:00 ሰዓት አካባቢ ነው።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሳፍሮ ወደ ደብረ ታቦር ይጓዝ የነበረና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-15146 ደቡብ የሆነው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በስፍራው ሲደርስ በመገልበጡ ከሞቱት በተጨማሪ 18 ቀላል እንዲሁም 4 ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በደጀን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና በደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ህይወታቸው ያለፈ ተማሪዎች አስከሬን ወደ ቤተሰቦቻቸው መላኩን አስረድተዋል።

ለጊዜው ከአካባቢው የተሰወረውን አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ማንኛውም የህዝብ ማመላለሻ በሌሊት እንዳይጓዝ በሁሉም ቦታ ቁጥጥሩ መጠናከር እንዳለበት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም