ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወጣቶች ከመንግስት ጎን መቆም አለባቸው - የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ወጣቶች ከመንግስት ጎን መቆም አለባቸው - የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2010 በአገሪቱ የተፈጠረው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ወጣቶች ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለባቸው የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት ገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሚነፍሰው የሰላም አየር የዜጎችን ዘላቂ ሰላም አንድነትና ትብብር እንዲያጎለብት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአገሪቱ እርቅ፣ ሰላምና መተሳሰብ እንዲጎለበት ወጣቶች ሃሳባቸውን በሰከነ መንገድ ማቅረብ ይገባቸዋል። ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች መንግስት ከወጣቶች ጋር የነበረው ግንኙነት ደካማ መሆኑን ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን ዴሞክራሲያዊና በሰለጠነ አካሄድ ማቅረብ እንጂ በስሜት ተገፋፍቶ ወደ አሉታዊ መንገድ መሄድ እንደሌለባቸው አሳስበዋል። የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅትም ከአንጋፋ እስከ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በማሰለፍ በአገሪቱ ሰላም፣ አንድነትና ፍትህ እንዲሰፍን ከመንግስት ጎን ይቆማል ብለዋል። በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት እንዲቻል በማድረግ በኩል ድርጅቱ አሻራውን እንዳሳረፈ አስታውሷል። ''ከኢትዮጵያም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም፣ መረጋጋትና ፍትህ እንዲሰፍን መንግስት የጀመረው እንቅስቃሴ እኛ ከተቋቋምንበት አላማ ጋር የሚዛመድ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን'' ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረውን የአንድነትና የእኩልነት መርህ እውን እንዲሆን ከመንግስት ጎን እንቆማለን ብለዋል።