የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን
ጎባ (ኢዜአ )መጋቢት 17/2012 የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ የጎባና አካባቢዋ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገልፇል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመግታት እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት በማስመልከት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የኃይማኖት አባቶች መካከል ሼህ አብዱሰላም ጣሂር እንደተናገሩት የእስልምና ኃይማኖት በአንድ አገር ውስጥ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ የራሱ የሆነ አስተምህሮት አለው ብሏል፡፡
አሁን የገጠመንን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመግታት በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች እየተሰጡ የሚገኙ መመሪያዎችና ምክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ህዝቡ በአግባቡ እንዲተገብር ሼህ አብዱሰላም አሳስበዋል ።
ምእማናኑን በማስተማር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጾዋል፡፡
ሀይማኖት ሳይለይ እየፈጀ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ህዝበ ክርስቲያኑ በጤና ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኘውን ትምህርት በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ራሱንና ወገኖቹን ከወረርሽኙ እንዲታደግ ያሳሰቡት ደግሞ በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሲናና ወረዳ አካባቢ ቤተክርስቲያን ኃላፊ ቄሲስ መኮንን ከተማ ናቸው፡፡
በርካታ ምዕመናን የሚያሳትፉ የትኛውም የአምልኮ ፕሮግራሞችና ሀይማኖታዊ ጉዞዎች ቅዱስ ሲኖዶሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረትተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል ፡፡
በጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚገለፁ ጥንቃቄዎች በተለይ እጅ መታጠብ፣አላስፈላጊ ንኪኪ ማስወገድ ፣ ማህበራዊ መራራቅ የመሳሰሉ መመሪያዎች ማክበር እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል ።
የሮቤ ከተማ አስተዳደር የሀገር ሽማግሌ ሀጂ አሎ ሁሴን በበኩላቸው ህዝቡ የራሱንና የአካባቢው ንጽህና እንዲጠብቅ በማስተማር ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል ።
የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሰለኝ ቱጁባ በበኩላቸው ህዝቡ ቫይረሱን ለመከላከል በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶእየሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።
የኃይማኖት አባቶች፣አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎችም ከግብረሃይሉ ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል ።
ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ ከ90 በላይ በሚሆኑ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ውስጥ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት የተዘጋጁ ሲሆን የጤና ባለሙዎች ስልጠናም ተሰጥቷል ።