የያኔት ሆስፒታል ባለቤት ያላቸውን ማዕከል ለኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና ህክምና እንዲያገለግል አስረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
የያኔት ሆስፒታል ባለቤት ያላቸውን ማዕከል ለኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና ህክምና እንዲያገለግል አስረከቡ
ሐዋሳ፤መጋቢት 17/2012 (ኢዜአ) በሐዋሳ ከተማ የሚገኘው የያኔት ሆስፒታል ባለቤት ያላቸውን የፅኑ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና ህክምና መስጫ እንዲያገለግል ለከተማ አስተዳደሩ አስረከቡ።
የሆስፒታሉ ባለቤት ዶክተር ግርማ አባቢ ማዕከሉን ዛሬ ለከተማው አስተዳደር ባስረከቡበት ወቅት ማዕከሉን ለፅኑ ህሙማን ይጠቀሙበት እንደነበርና 80 አልጋዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱ እንደ ሀገር ሊያስከትል የሚችለው ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ከግምት በማስገባት ለኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና ህክምና መስጫ እንዲያገለግል ማስረከባቸውን ተናግረዋል።
ይህንን ያደረጉት በራሳቸው ተነሳሽነት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ግርማ፤ በሙያቸውም እስከ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
"ሁላችንም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ባለን አቅም ከመንግስትና ከህዝብ ጎን ልንቆም ይገባናል" ያሉት ዶክተር ግርማ
በማዕከሉ ክትትል እየተደረገላቸው የነበሩ ህሙማንም ወደ ተዘጋጀላቸው ተለዋጭ ቦታ እንደሚሄዱ አመልክተዋል።
የማዕከሉ መታከሚያ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ የተገነቡና ለህክምና አገልግሎት ምቹ እንደሆኑም ተመልክቷል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በከተማው እስካሁን አንድ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ብቻ መኖሩን ጠቁመው፤ ካለው ዓለም አቀፍ ሥጋት አንፃር ይህ በቂ ባለመሆኑ የመንግስት ጤና ተቋማትን በማስለቀቅ ለዚህ ዓላማ የማዘጋጀት ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ግርማ ከማንኛውም ነገር በላይ ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለሌሎችም አርአያ እንደሆኑ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
ማዕከሉን ቫይረሱ ከሀገር መጥፋቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ እንዲጠቀሙበት በመፍቀዳቸው አመስግነው ይህም በሽታውን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት በሽታውን ከመከላከልና ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የከተማዋን ባለሀብቶችንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የሃብት አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማ እስካሁን አንድም ሰው በቫይረሱ እንዳልተያዘ ከምክትል ከንቲባው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።