የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሆስፒታል ለኮሮና ተጠርጣሪዎች ማቆያና ማከሚያ እንዲውል ተወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሆስፒታል ለኮሮና ተጠርጣሪዎች ማቆያና ማከሚያ እንዲውል ተወሰነ
ድሬዳዋ/ኢዜአ/መጋቢት 17/2012 በድሬዳዋ የሚገኘውና በተለምዶ የፈረንሣይ ሆስፒታል በሚል የሚታወቀው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሆስፒታል ለኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች ማቆያና ማከሚነያት እንዲውል የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ተረከበው ።
የድሬዳዋ አስተዳደር በተናጠልና ከተጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር መለስተኛ ሆስፒታል የሚሰጣቸውን ሌሎች አገልግሎቶች በመተው ለኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች ማቆያና ማከሚያነት እንዲውል አድርጓል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የድሬዳዋ ጤና ቢሮ አመራሮችና ሐኪሞች በሆስፒታሉ የተከናወኑትን ዝግጅቶችን ተመልክተዋል፡፡
የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር እንደገለፁት ድሬዳዋ በመልከአ ምድራዊ አቀማመጧ ፣ ለጎረቤት ሀገራት ካላት ቅርበት፣ የንግድ ማእከልና ማህበራዊ መስተጋብር የምታስተናግድ በመሆኗ ለቫይረሱ ተገላጭነቷ ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
ይህንኑ የሚመጥን የመከላከል ሥራ በተናጠልና ከተጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት በጅቡቲ-ደወሌ-ድሬዳዋ ፈጣን መንገድ ፣ በምድር ባቡርና በድሬዳዋ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግዋል፡፡
ከመከላከሉ ሥራ ጎን ለጎን ለኮሮና ቫይረስ ተጠርጣሪዎች ለይቶ ማቆያነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎችና የህክምና ቁሶች የተሟሉለት ጤና ጣቢያ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ዛሬ የተረከቡት የኢትዮ ጅቡቲ ሆስፒታልም ሊመጣ የሚችለውን ጉዳትና ችግር ለመቀነስና ለመቆጣጠር ሰፊ አበርክቶ እንዳለው ነው የገለፁት፡፡
በግል ጤና መስጫ ተቋማትም ተመሣሣይ ለይቶ ማቆያ ስፍራ እንዲዘጋጅ መመሪያ ተላልፏል ብለዋል፡፡
በከተማው የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሶች እንዲሟሉ ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው መድኃኒት አቅራቢ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ፉአድ ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ ነዋሪው ስለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ሊደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ኪሳራ መከላከል እንዳበት አሳስበዋል፡፡