በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ጤናቸው እየተመለሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ጤናቸው እየተመለሰ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2012( ኢዜአ)በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) የተያዙ ሰዎች በሚሰጣቸው የህክምና አገልግሎት ጤናቸው እየተመለሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ ።
በኢንስቲትዩቱ የኮሮናቫይረስ ምላሽና ቁጥጥር የኢንፌክሽን ዩኒት አስተባበሪ አቶ ጌታነህ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ የህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው።
ለበሽታው ይህ ነው የሚባል መድሃኒት ባለመኖሩ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሚሰጣቸው ድጋፍ ጤናቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ በበቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የከፋ የጤና ችግር እንዳላጋጠማቸውና በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በቤት ውስጥ ቆይተው ህመማቸው የከፋ ደረጃ ሳይደርስ ወደ ህክምና ተቋም መምጣታቸው ጤንነታቸው እንዲሻሻል እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በዚህም ማህበረሰቡንና በሽተኞችን ከከፋ ጉዳት መታደግ የተቻለ ሲሆን ህብረተሰቡ የበሽታው ምልክት ሲያጋጥም ፈጥኖ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ የቫይረሱ ምልክት ለታየባቸውና በበሽታው ለተያዙ የህክምና አገልግሎት መስጠቱ እንዳለ ሆኖ ዋናው ትኩረት ስርጭቱን መግታት ነው።
በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር እስካሁን 12 ሲሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደረግ የቁጥር ለውጥ ሲኖርም እንደሚነገር ነው የጠቆሙት።
በአዲስ አበባ የየካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በበሽታው ለተያዙና ምልክት ለታየባቸው ሰዎች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ሌሎች ሆስፒታሎችም ለአገልግሎት እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የበሽታውን ስርጭት መግታትና መከላከል ዋናው መድሃኒት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በአግባቡ እንዲተገብርም አስተባባሪው መክረዋል።
የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በኮሮናቫይረስ 18 ሺህ 589 ሰዎች መሞታቸውንና 416 ሺህ 686 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ከ114 ሺህ በላይ ደግሞ ከቫይረሱ አገግመው ጤናቸው ተመልሷል።
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 12 የደረሱ ሲሆን እስካሁን ህይወታችው ያለፈ የለም።
ደረቅ ሳል፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታት ከበሽታው ምልክቶች መካከል ሲሆኑ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት በሽታው የሚተላለፍ በመሆኑ፤ እጅን በሳሙና እና ውሃ በደንብ መታጠብ እንዲሁም ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ከመከላከያ መንገዶች ውስጥ መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።