ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ጋምቤላ/ ሀዋሳ (ኢዜአ) መጋቢት 17/2012 ፡- በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኃይማኖት አባቶች የአጋርነት ሚናቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጠየቁ፡፡
የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

ርዕሰ መሰተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚቻልባቸው ጉዳዮችን አስመልክተው ትናንት በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን አነጋግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከል መንግስት ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ለቫረሱ ስርጭት የህዝብ መተፋፈግና መቀራረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ በእምነት ተቋማት ይህ ሁኔታ እንዳይኖር የሃይማኖት አባቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል እንደ ሀገር በተቀመጡት አቅጣጫዎች መሰረት የተለያዩ ግብረ ሃይሎችን በማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከሃይማኖት አባቶች መካከል ፓስተር ፒተር አግዋ በሰጡት አስተያየት በመንግስት የሚተላለፉ መመሪያዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ የድርሻው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በተለይም ቀደም ሲል ተፋፍጎና ተቀራርቦ ሲካሄድ የነበረውን የአምልኮ ስርዓት በማስቀረት በተራራቀ መልኩ የፀሎት ስርዓታቸውን እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።

የቫይረሱን ወርርሽኝ ለመከላከል የተቻለቸውን ሁሉ አስተዋፅኦ ለማበረከት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ አባ መላከ ኃይለምህረት ይማም ናቸው። 

ሌላው አባት ፓስተር ኡሞ ኡዎሪ እንዳሉት ደግሞ ቫይረሱ በዓለም እያደረሰ ያለውን እልቂት በመገንዘብ በሽታውን ለመከላከል ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከአነጋገሩዋቸው የእምነት ተቋማት ተወካዮች መካከል የኢትየጵያ እርቶዶክ ተዋህዶ፣የመካነ እየሱስ ፣ የአድቨንቲስትና ሌሎችም ይገኙበታል።

በተመሳሳይ መልኩ የደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የጀመራቸውን ጥረቶች በመደገፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል ።

ጉባኤው የሀይማኖት ተቋማትና ህዝበ ምዕመኑ ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል ።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅና የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መጋቤ ጥበባት ቄሲስ ሞላልኝ መርጊዶ ቫይረሱ ዘርና ሀይማኖት ሳይለይ የሰው ልጅ እየፈጀ እንደሚገኝ ገልፀው ምዕመኑ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል ።

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ሸርዐ ፍርድ ቤት ዋና ቃዲና የክልሉ የእስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ተወካይ ሼክ አብራር ሽፋ በበኩላቸው ይህ የችግር ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ህዝበ ሙስሊሙ የተሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ጣልቾ በበኩላቸው ህዝቡ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በመራራቅ ፥እጅ ባለመጨባበጥና አልኮልና መሠል በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በመከተል ተገቢውን የመከላከል ስራ እንዲያከናውን መክረዋል ።

በመግለጫው ወቅት የተገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ህዝብ ተሰብስቦ በየእምነት ተቋማቱ የሚያከናውኑዋቸው  የአምልኮ ስነ ስርዓቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ መስማማታቸውን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም