ቀጥታ፡

ከአየር መንገድ ጠፍተው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅዋል የተባሉ ግለሰቦች የገቡት የግዴታ ለይቶ ማቆየት ከመተግበሩ በፊት ነው - የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2012 (ኢዜአ)  ከአየር መንገድ ጠፍተው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅዋል የተባሉ ግለሰቦች የገቡት የግዴታ ለይቶ ማቆየት ከመተግበሩ በፊት መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ወደ ለይቶ ማቆያ ሳይገቡ ከአየር መንገድ ጠፍተው ወጡ በሚል የተጠቆሙ ግለሰቦችን ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ማንኛውም ከውጭ አገር የሚመጣ መንገደኛ በተመረጡ ሆቴሎች ውስጥ በራሱ ወጪ ለ14 ቀናት ተለይቶ እንዲቆዩ የተወሰነ መሆኑ ይታወቃል።

ሆኖም መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ አንድ መንገደኛ ወደ አገር ከገቡ በኋላ ከአየር መንገድ በመጥፋት ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለዋል በሚል በማሕበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው እና የበርካታ ሕብረተሰብ ስጋት የሆነው የአንዲት ግለሰብ ስም ለጤና ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተደጋጋሚ ጥቆማ መድረሱን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተሰጠውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ማጣራት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።

የተጠቀሱት ግለሰብ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ግለሰቦቹም ወደ አገር ሲገቡ በቦሌ አለም ዓቀፍ አየር መንገድ የሚደረገው የልየታ ሂደት ውስጥ ማለፋቸውን መረጋገጡን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ የገቡት የግዴታ ለይቶ ማቆየት ከመተግበሩ በፊት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ በቀጣይም ከሕብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን በመቀበልና በማጣራት ተግባራዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።

ማሕበረሰቡ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ የሆኑትን የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚሰጡትን ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ በመከተል እና በመጠቀም ኮቪድ-19ን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በተረጋጋ አካሄድ እንዲያግዝ ዶክተር ሊያ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም