'ምዕምኑ በሬን እዘጋለሁ፤ ፈጣሪዬን አምናለሁ' በሚል መርህ በመመራት ራሱን ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቅ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
'ምዕምኑ በሬን እዘጋለሁ፤ ፈጣሪዬን አምናለሁ' በሚል መርህ በመመራት ራሱን ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቅ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ መጋቢት 16/2012(ኢዜአ) 'ምዕምኑ በሬን እዘጋለሁ፤ ፈጣሪዬን አምናለሁ' በሚል መርህ በመመራት ራሱን ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አሳሰበ።
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ጥንቃቄ እንዲደረግ በእየእምነት ተቋማቱ ጥሪ ቢተላለፍም በምዕመኑ ዘንድ የሚስተዋለው የጋራ አምልኮ ለቫይረስ መዛመት ስጋት ማሳደሩም ተጠቁሟል።
ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በሩብ ዓመት ብቻ 195 አገራትን በማዳረስ ከ400 ሺህ በላይ ዜጎችን ለህመም በመዳረግ አገራትን ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርጓል።
የመድኃኒትም ሆነ ክትባት መላ ያልተገኘለት ቫይረሱ ድህነት በበረታባቸውና ማኅበራዊ አኗኗራቸው የተጠጋጋ ህዝቦች ባሉባቸው አገራት ደግሞ ከተዛማችነት ባህሪ አኳያ ስጋቱ ይበልጥ ተደቅኖባቸዋል።
ከድህነቷ ባሻገር ከ97 በመቶ ህዝቧ አማኝ እና የህዝቡ ማህበራዊ ሕይወትም የተሳሰረ በሆነባት አትዮጵያ በተለይ በሃይማኖት ተቋማት አካባቢ ያለው የምዕመን አምልኮ ስርዓት ለቫይረሱ መዛመት ዕድል ይፈጥራል።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ስርዓቶች ጥንቃቄ በተሞላበትና መንግስት ከወሰነው ድንጋጌ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲካሄዱ በክርስትናም ሆነ በእስልምና የበላይ ተቋማት መመሪያ መሰጠቱ ይታወሳል።
ኢዜአ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዓለምን ባዳረሰው መቅሰፍት ህዝቡ ማመን ብቻ ሳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መመሪያ ቢወርድም በየእምነት ቦታዎች ያለው ተፈጻሚነት ግን ክፍተት እንዳለበት ነው የገለጹት።
በዚህም በየገዳማትና አድባራት፣ በመስጊዶችና በአምልኮ ስፍራዎች በምዕመኑ ዘንድ የሚስተዋለው ስነ ስርዓት ለቫይረሱ መዛመት ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
በማህበራዊ ግንኙነት ረገድ ከኢትዮጵይ ህዝብ ጋር ተመሳሳይ ባህል ባላት አገረ ጣሊያን የካቶሊክ ሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በቫይረሱ ተጠቅተው መሞታቸውን አስታውሰው፣ የጥንቃቄ መመሪያው ገቢራዊ ካልሆነ በኢትዮጵያም ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ብለዋል።
በዚህም ምዕመኑ 'ቤቴን እዘጋለሁ፤ ፈጣሪዬን አምናለሁ' በሚል መርህ በመመራት ራሱን ከቫይረሱ ሊጠብቅ እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ሰባት የሃይማኖት ተቋማትን ያቀፈው ጉባኤው ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመገኘቱ ቀደም ብሎ ተቋማቱን በማስተባበር ለምዕመናኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እንዲሰጡ ማድረጉን አንስተዋል።
በቤተ እምነቶች ቁርጠኝነት ቢኖርም በታችኛው የቤተ እምነት አመራሮች ዘንድ ያለው ተፈጻሚነት ችግር እንዳለ የጠቆሙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፣ "ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል" በለዋል።
ለአብነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ በቅዳሴ ስርዓት ተሳታፊዎች እንዳይሄዱ፣ አውደ ምህረትና ሌሎች የምህላ ስነ ስርዓቶች ለጊዜው እንዲቋረጡ ቢታዘዝም ተፈጻሚነቱ ላይ ችግር እንዳለ አንሰተዋል።
በመስጊድ የሚደረግ ስግደትም እንዲቆም በእምነት ተቋሙ ውሳኔ መሰረት የመስጊድ ኢማሞች ትዕዛዙን ገቢራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ይህ የፈተና ወቅት ህዝቡ ፈጣሪውን ምህረት በመጠየቅ በየቤቱ ማሳለፍ እንዳለበትም ጠይቀዋል።
ለምዕመኑ ግንዛቤ በመስጠት በኩል መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች ሊተባበሩና ኃፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ተብሏል።