ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንበረ ፓትሪያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንበረ ፓትሪያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ
አዲስ አበባ መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ፓትሪያርክና መላው አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በኮረናቫይረስ ምክንያት በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ።
ውሳኔው ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ሲኖዶሱ መወሰኑን ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ የወሰነውን ውሳኔ አስመልክልቶ በመንበረ ፓትሪያርክ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅና የአርሲ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ያሬድ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።
በዚህም ለአስቸኳይ ስራ ከሚፈለጉና ተለይተው እንዲቆዩ ከሚደረጉ የጽህፈት ቤት ሰራተኞች በስተቀር የጠቅላይ ጽህፈት ቤቶችም ሆነ የመላው አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ስራዎቻቸውን በየቤታቸው ሆነው እንዲያከናውን ወስኗል።
ቋሚ ሲኖዶሱ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ከነገ ጀምሮ ለስራ ሲፈለጉና ጥሪ ሲደረግላቸው ከሚመጡት በስተቀር ሁሉም በየቤታቸው እንዲቆዩ መወሰኑን ሊቀ ጳጳሱ አረጋግጠዋል።