ቀጥታ፡

ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በለይቶ ማቆያ ያሉ ዜጎች በሃኪሞች ክትትል እየተደረገላቸው ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2012(ኢዜአ) ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ለገቡና በለይቶ ማቆያ ላሉ ዜጎች የህክምና ባለሙያዎች ተመድበው ክትትል እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ መንግስት በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ30 አገራት የሚያደርገውን በረራ ማቋረጥ፣ ሰዎች የሚዘዋወሩባቸው የየብስ ድንበሮችን መዝጋት፣ ትልልቅ ስብሰባዎችን መከልከል፣ የትምህርት ተቋማትን መዝጋት ለአብነት ይጠቀሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት የሚመጡ ሰዎች ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ፤ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሄድ የኢትዮጵያን ምድር የሚረግጡ ሰዎችም ከኅብረተሰቡ ጋር ሳይቀላቀሉ በለይቶ ማቆያ እንዲስተናገዱ መወሰኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ጌታነህ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በበርካታ የዓለም ሀገራት ተዳርሷል።

በመሆኑም ስርጭቱን ለመቆጣጠር ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚመጡ ዜጎች የህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶች በተሟሉበት የለይቶ ማቆያ ስፍራ እንዲስተናገዱ ይደረጋል ብለዋል።

ዜጎች ወደ ለይቶ ማቆያ ከገቡ በኋላ በሰዓታት ወይም በቀናት ልዩነት ምልክቶች ሊታዩባቸው ስለሚችሉ በፍጥነት ወደ ህክም ለመውሰድ ያግዛል ብለዋል።

ከሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በስካይ ላይት እና ግዮን ሆቴሎች በቂ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የግዮን ሆቴሎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረፃድቃን አባይ፤ በግዮን ሆቴል ለሚገኑ ከ150 በላይ ዜጎች  ሶስት የህክምና ባለሙያዎች ጊዜያዊ ቢሮ ተሰጥቷቸው በየቀኑ ክትትል እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በለይቶ ማቆያ ቦታዎች ካሉት አንዳንዶቹ "ሙቀታችን በየጊዜው አይለካም፤ በቂ ክትትል አይደረግልንም " በማለት ቅሬታቸውን አንስተዋል።

የኢንስቲትዩቱ የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ጌታነህ አብረሃ ከአስተያየት ሰጭዎቹ የሚቀርበውን ቅሬታ እንደግብዓት እንወስዳለን ብለዋል።

ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ ወዲያውኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው እንደ ኩላሊትና ሌሎች የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ስለሚኖሩ በቅርበት ክትትል እያደረግን መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል።

በሽታው ከተከሰተባቸው ሀገሮች መምጣታቸው እየታወቀ ቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉ ዜጎች ስለመኖራቸው የተጠየቁት አቶ ጌታነህ "በጭራሽ ማንም የለም" ሲሉ መልሰዋል።

ከየትኛውም የዓለም ክፍል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ስለሚያዳግት ሁሉም ኳራንታይን መግባት አለባቸው ብለዋል።

በሥራ ሂደት ችግሮች ይኖራሉ፤ ነገር ግን በሽታው ይኑርበት አይኑርበት በምርምራ መረጋገጥ ስላለበት ቀጥታ ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀል አንድም ሰው አይኖርም ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም