ከአፍሪካ አገሮች ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ስኬታማ ዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይቻላል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ከአፍሪካ አገሮች ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ስኬታማ ዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ይቻላል-ምሁራን
አዲስ አበባ፣መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን እንደምትችል ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ድርድር አሰላለፏን በየጊዜው እየቀያየረች በምትቀርበው ግብጽ አማካኝነት 'አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ' እያለ እስካሁን ያለስኬት ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ በነበረው ድርድር የቀረቡ ሃሳቦች "ብሔራዊ ጥቅሜን የሚጎዱ ናቸው" በማለት በይፋ እረሷን ከድርድሩ ማግለሏ ይታወሳል።
"አሜሪካ ግድቡን በሚለከት ሚዛናዊ ያልሆነ አቋም አንጸባርቃለች" ስትልም በይፋ ቅሬታ አቅርባለች።
ይህን ተከትሎም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ 'ደጋፊ ለማሰባሰብ' በሚል ወደ ተለያዩ አገራት በማቅናት "ግድቡ የግብጽን ጥቅም ይጎዳል" ሲሉ ሰብከዋል።
ኢዜአ በግድቡ ዙሪያ የሚከናወነውን የዲፕሎማሲ ስራ በሚመለከት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰር የሆኑት ጣሰው ወልደሃናን እና የጅኦ-ፖለቲካ ምሁሩን ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰን አነጋግሯል።
ፕሮፌሰር ጣሰው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከተለያዩ አገራት ጋር ጥሩ የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፈጥራለች።
ነገር ግን ይህ ግንኙነት ወደ ጠንካራ ወዳጅነት መቀየር የሚችለው የዳበረ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር መሆኑን ነው የገለጹት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በተለይ ከአፍሪካ አገራት ጋር የጎለበተ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከጎኗ እንዲቆሙ ማድረግ ትችላለች ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ እድሎችን ለህዳሴው ግድብ ዲፕሎማሲ አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ትልቁ የዲፕሎማሲ አጀንዳ ግድቡ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የጅኦ-ፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በበኩላቸው ግብጻውያንን ግድቡ የሚጎዳቸው አስመስሎ በማቅረብ ረገድ ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተቃራኒው ኢትዮጵያ ያለውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቅ አንጻር በሚፈለገው ደረጃ እየተንቀሳቀሰች አይደለም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ጠንካራ ግንኙነት ለግድቡ ዲፕሎማሲ ቀጣይነት ባለው መልኩ መጠቀም እንደሚገባም መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከራሷ በተጨማሪ ለአካባቢው አገራት የሃይል አማራጭ ለመፍጠርና የመሰረተ ልማት ትስስር እውን ለማድረግ ጥረት በማድርግ ላይ ትገኛለች።
በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው አገራት ጉልህ ጠቀሜታ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሁናዊ አፈፃፀም 71 በመቶ ደርሷል።