ቀጥታ፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ 20 በመቶ ሠራተኞቹ ብቻ በቢሮ ሥራ ላይ አንዲገኝ ወሰነ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2012(ኢዜአ)የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ 20 በመቶ ሠራተኞቹ ብቻ በቢሮ ሥራ ላይ እንዲገኙ መወሰኑን አስታወቀ። 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተቋማቸው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መንግሥት ባወጣው አሰራር መሰረት ተግባራዊ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ተቋሙ አሁን ካሉት ሠራተኞች 20 በመቶ ብቻ በቢሮ ሥራቸው እንዲገቡና ቀሪዎቹ ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ተወስኗል ነው ያሉት።

በቢሯቸው እንዲሰሩ የተደረጉት ሠራተኞች ተቋሙ የሚሰጣቸውን ዋና ዋና አገልግሎቶች ብቻ በመፈጸም ሥራ እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ኃይል መሆኑንም አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ዳይሬክተሮች የማኔጅመንት አባላትና ባለሙያዎች ትራንስፖርት ቀርቦላቸው እንዲሁም  በምቹ የሥራ ሁኔታ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

መዝገብ በእጃቸው የሚገኝ የሕግ ባለሙያዎች ሥራቸውን እንዲያጠናቅቁ በቢሮ እንዲገኙ መወሰኑንም ገልጸዋል።

የሥራ ጫናና የሠራተኞቹ አስፈላጊነት ታይቶ አንዳንድ ሠራተኞች እንደ አስፈላጊነቱ ከቤታቸው ተጠርተው ሥራቸውን እንዲከውኑ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በቤታቸው ሥራቸውን የሚያከናውኑ ሠራተኞች ሥራዎችን በኢሜይልና በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች በመለዋወጥ አገልሎቱ እንዲቀጥል ያደርጋሉ ብለዋል።  

በሌላ በኩል ለማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ እንደነበር አስታውሰው ሥልጠናው እንዲቋረጥ መወሰኑን ተናግረዋል።

የተቋሙ የሕግ ባለሙያዎች ሥልጠናም በተመሳሳይ መቋረጡንና ወሳኝ የሆኑ የሕግ ምርምር ሥራ ላይ በጊዜያዊነት ትኩረት እንዲደረግ  መወሰኑን ገልጸዋል።

የሰነዶች ማረጋገጫ ጽህፈት ቤትም አሁን ላይ የውክልና መስጠት አገልገሎት ላይ ብቻ እንዲወሰን መደረጉንና  ይህም በኦላይን የታገዘ አሰራር መሆኑን ጠቅሰዋል።  

ጎን ለጎንም አነስተኛ የንግድ ማኅበራትን (ከ50 ሰዎች በታች አባላት ያሉት) ለመመሥረት የሚቀርቡ ጥያቄዎችም አገልግሎቱ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ ምዝገባ ለጊዜው መቋረጡን ገልጸው ሌሎች ተጓዳኝ አጫጫር ሥራዎች ብቻ ተለይተው አገልግሎቱ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም