ቀጥታ፡

ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና 64 ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸው አለፈ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ውስጥ የነበሩ 64 ኢትዮጵያዊያን ታፍነው ህይወታቸው አለፈ። 

በጭነት መኪናው ታፍነው ህይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ 14 ሰዎች በህይወት መገኘታቸውም ታውቋል።

"የሞዛምቢክ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሰራተኞች የጭነት መኪናውን ሞአትዜ በተባለችው የግዛቲቱ ከተማ ውስጥ አስቁመው ሲፈትሹ ነው ሟቾቹን ያገኙት" ሲሉ የቴቴ ክፍለ ሃገር የጤና ሃላፊ ካርላ ሞሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።  

ባለስልጣኗ እንዳሉት በጭነት መኪናው ላይ የተሳፈሩት ሰዎች ህይወታቸው በምን ምክንያት ሊያልፍ እንደቻለ ምርመራ እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያዊያኑ ህይወት ያለፈው በመኪናው ውስጥ በአየር ማጣት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።  

የሞዛምቢክ ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አገልግሎት ቃል አቀባይ አሜሪያ ደሪዬሮ እንደተናገሩት ሟቾቹን ያሳፈረው የጭነት መኪና ሾፌር እንዲቆም ሲጠየቅ ፍላጎት አልነበረውም ብለዋል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ውስጥ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ህይወት ማለፉን ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማረጋገጡን አስታውቋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢፌዲሪ ኤምባሲ እና በሞዛምቢክ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ጋር በቅርበት እየሰራ ሲሆን ፤የሟቾቹን ብዛት እና መሰል ዝርዝር መረጃዎችን በተመለከተ በቀጣይ የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጾል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም