የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2010 የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 3ሺህ189 ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያስተማራቸውን ሶስት ተማሪዎችንም አስመርቋል። በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንደገለጹት፤ ተመራቂ ተማሪዎች ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ውስጥ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ተመራቂዎቹ የከተማዋን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን በተማሩት ሙያ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ የዜግነት ድርሻቸውን በንቃት እንዲወጡ አሳስበዋል። በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ምክንያታዊና ዴሞክራሲያዊ አመለካከት እንዲጎለብት፣ በታማኝነትና ከልብ በመነጨ የአገር ፍቅር ስሜት ህዝብን ማገልገል እንዳለባቸው አቶ አባተ አስገንዝበዋል። ዩኒቨርሲቲው ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ዋነኛ ተዋናይ የሆነውን የሰው ኃይል በእውቀትና በክህሎት በማነጽ አገራዊ እድገትን የሚያስቀጥል ትውልድ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል ምንጭ ከመሆን ባለፈ የከተማዋን ቁልፍ ችግሮች የሚዳስስ የጥናትና ምርምር ማዕከል በመሆን አማራጭ መፍትሄ የሚያፈልቅ ተቋም መሆን እንደሚጠበቅበት ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩም ለዩኒቨርሲቲው መጠናከርና ማደግ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች መመረቅ ማለት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ በማወቅ ሁሌም ማንበብ፣ መመራመርና ለቀጣይ የትምህርት እርከን ራስን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቷ የለውጥ፣ የፍቅርና የብሔራዊ አንድነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሆነች ጠቅሰው ተመራቂ ተማሪዎች የለውጡ አካል በመሆን የሚጠበቅባቸውን የትውልድ ተልዕኮ በጽናት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል። በተለይም ዘንድሮ የለውጥና የመደመር ታላቅ አገራዊ ንቅናቄ የተካሄደበት መሆኑን ተናግረው ተመራቂ ተማሪዎች በመጪው ዘመን ይህንን የፍቅር፣ የመተሳሰብና የመደመር ጽኑ ስሜት ይዘው ለአገሪቱ እድገት በተሰማሩበት የሥራ መስክ እንዲረባረቡ አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ ዓመት በቅድመ መደበኛ፣ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቀ ሲሆን ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 54 በመቶ ሴቶች ናቸው። ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው ሴት ተማሪዎች ቁጥር መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የቀየሰውን ስትራቴጂ ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተገበረ ስለመሆኑ የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል።