የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የእምነት ተቋማት ያሳለፉትን ውሳኔ ተከታዮቻቸው ማክበር እንዳለባቸው ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የእምነት ተቋማት ያሳለፉትን ውሳኔ ተከታዮቻቸው ማክበር እንዳለባቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የእምነት ተቋማት ተከታዮቻቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ያወጧቸውን ውሳኔዎች ተፈጻሚነት መከታተል እንዳለባቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጻሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሁሉም የኃይማኖት ተቋማት በሽታውን ለመከላከል ለምዕመናኑ ውሳኔዎችን ማስተላለፋቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንን ጨምሮ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ለተከታዮቻቸው ለጥንቃቄ የሚያግዙ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
ይሁን እንጂ በተወሰነ መልኩ ምዕመናን ራሳቸውን ለወረርሺኙ በሚያጋልጥ መልኩ ኃይማኖታዊ ክዋኔዎችን እያደረጉ መሆኑን ሊቀ ትጉሃን ተናግረዋል።
ምዕመናኑ በጤና ባለሙያዎች በኩል ከተላለፉት የጥንቃቄ መልዕክቶች መካከል ከፍተኛ የሰዎች ስብስብን መቀነስ አንዱ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ገና ይቀራል ብለዋል።
''የሃይማኖት ተከታዮች አንድ ላይ ተሰብስበው ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ማከናወናቸው ጎጂ መሆኑን ሊያውቁና ሊጠነቀቁ ይገባል'' ነው ያሉት።
ምዕመኑም ከጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ለሚተላለፉት የጥንቃቄ መልዕክቶች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የእምነት ተቋማት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች ተከታዮቻቸው ተግባራዊ ማድርጋቸውን መከታተል አለባቸው ተብሏል።