ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል 20 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመላ አገሪቱ ሊሰማሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ" የኮሮናቫይረስን ለመከላከል 20 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በመላ አገሪቱ ሊያሰማራ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም የዓለም ስጋት የሆነው የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያም ውስብስብ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል ከወዲሁ የመከላከል ስራ ለመስራት በጎ ፈቃዳኛ ወጣቶችን ሊያሰማሩ መሆኑን ጠቁሟል።

በመርሃ ግብሩ ከ9 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች በመላ አገሪቱ እንዲሰማሩ ይደረጋል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ወጣቶቹ ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ወጣት ብርሃኑ ገልጿል።

ለበጎ ፋቃድ አገልግሎት የሚሰማሩት ወጣቶች ህዝቡ ከኮሮናቫይረስ ራሱን እንዲጠብቅና እንዲከላከል ግንዛቤ ከመፍጠር በተጓዳኝ ህገ-ወጥ ተግባራትን የመከላከል ተልእኮ ይሰጣቸዋል።

አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋደዎችንና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ከፖሊስ ጋር በመተባበር የመከላከልና የቁጥጥር ስራ የሚያከናውኑ ይሆናል።

አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች በአዲስ አበባ አምስቱም መገቢያና መውጫ በሮች ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁሟል።

የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ዜጎች የማድረስ ስራ የሚያከናውኑ መኖራቸውንም እንዲሁ።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለው የዘመቻ እንቅስቃሴ እንዲቀላቀሉ ሊጉ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ከዚህ ቀደም በአረንጓደ ልማት መርሃ ግብር በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፉንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም