ቀጥታ፡

ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትና ችግረኛ ዜጎች የሚረዱበት የአጭር መልዕክት ኮድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትና ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመርዳት የሚያስችል የተንቀሳቃሽ ስልክ አጭር መልዕክት ኮድ /6650 A/ ይፋ አደረገች። 

የድጋፍማሰባሰቢያቁጥሩን ይፋ ያደረገው የቤተክርስቲያኗ የህጻናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ነው።     

ድርጅቱ ለኢዜአ የላከው መግለጫ በ1965 ዓ.ም መቋቋሙንና ምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታልን ጨምሮ በ18 ማዕከላት ችግረኞችን በመርዳት ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ይህ ድርጅት 4 ሺህ 395 ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በማዕከላቱ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች በመርዳት ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም 22 ሺህ 648 ህጻናትና ችግረኛ ቤተሰቦችንም በተዘዋዋሪ ይረዳል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከውጭ ረጂዎች ይገኝ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ በመምጣቱ እነዚህን ወገኞችን ማገዝ የሚያስችል የአቅም ውስንነት መፈጠሩን ጠቅሷል።  

ለዚህም ድርጅቱ አዲስ ዕቅድ በመንደፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የዚህ ሰናይ ምግባር ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚላክ አጭር መልዕክት ቁጥር ይፋ ማድረጉን አስታውቋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚሁ ዓላማ በተከፈተው የአጭር መልዕክት ቁጥር 6650 ላይ A ብሎ በመላክ 3 ብር ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ድርጅቱ ባለፉት 46 ዓመታት ከ42 ሺህ በላይ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በማሳደግ ለቁም ነገር ማብቃቱን ገልጿል።

ድርጅቱ በቤተክርሲቲያኗ አዋጅ ቁጥር 404/1960 እና በአዲሱ የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር በምዝገባ ፍቃድ 0631 የተመዘገበ ሰብዓዊ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም