ሆስፒታልና ማረሚያ ቤት ተመላላሽ ታካሚዎችንና ጠያቂዎች እንዳይገቡ ታገደ - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታልና ማረሚያ ቤት ተመላላሽ ታካሚዎችንና ጠያቂዎች እንዳይገቡ ታገደ
ጎንደር/ደሴ ኢዜአ 14/07/ 2012 በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በከተማው ማረሚያ ቤት ኮሮናን ለመከላከል ተመላላሽ ታካሚዎችንና ጠያቂዎች እንዳይገቡ ላልተወሰነ ጊዜ ታገደ፡፡
የወሎ ዩኒቨርስቲም ለተማሪዎች ደህንነት ሲባል ከግቢው መውጣትም ሆነ መግባት ክልከላ ማስቀመጡን ገልጿል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ለኢዜአ እንደተናገሩት ከድንገተኛ ጉዳቶች ውጭ ለአዳዲስና ቋሚ ተመላላሽ ታካሚዎች ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡
ሆኖም ክትትል የሚያስፈልጋቸው የስኳር፣ የልብ፣ የደም ግፊትና ካንሰር በሽታ ያለባቸውን ታካሚዎች ክልከላው አያካትትም፡፡
በቀን ከአንድ ሺህ 200 በላይ ተመላላሽ ታካሚዎችና እስከ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ጠያቂዎች በሆስፒታሉ ይመጡ እንደነበር የገለጹት ዶክተር አሸናፊ አሁን በበሽታው ስጋት ምክንያት እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በሆስፒታሉ ተኝተው ለሚታከሙ አንድ አስታማሚ መታወቂያ ካርድ በመጠቀም መግባት ይችላል ብለዋል።
ድንገተኛ ጉዳት የደረሰባቸውና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችም የግድ ከሆነ በመለየት ይስተናገዳሉ፡፡
በጎንደር ከተማ የአንገረብ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ታራሚን ለመጠየቅ የሚመጡ ቤተሰቦችንና ከፖሊስ ጣቢያ ወደ ማረሚያ ቤት የሚዛወሩ ታራሚዎች እንዳይመጡ መከልከሉን አስታውቋል።
በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የመሰረታዊ ፍላጎትና ጤና አገልግሎት ቡድን መሪ ኮማንደር በለጠ ላቀው እንዳሉት ከመከልከሉ በፊት በየቀኑ ከ300 በላይ የታራሚ ቤተሰቦች ወደ ማረሚያ ቤቱ ይመጡ ነበር።
ታራሚዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚገቡ ህግ አስከባሪዎችና ሌሎች ሰራተኞች ከመግባታቸው በፊት ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው፡፡
ታራሚዎች አኗኗራቸው ምን መሆን እንዳለበት፣ በግልና በአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫረስን ለመከላከል ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡና እንዳይገቡ መከልከሉን የዩኒቨርስቲው የህዝብ ግንኙነት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ አሰፋ አስታውቀዋል።
ለተማሪዎች ደህንነት ሲባል ክልከላው ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በየተማሪዎች ማደሪያ፣ ካፌዎችና አልፎ አልፎ ተማሪ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የንጽህና መጠበቂያ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ውሃና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችም ተቀምጠው እጃቸውን እንዲታጠቡ እየተደረገ ነው፡፡
ትምህርታቸውንም በየማደሪያ ክፍሎቻቸው እንዲከታተሉ መምህራንም ባሉበት ሆነው አስፈላጊውን መረጃ እዲያደርሷቸው የኦላይን ትምህርት መጀመሩን ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መንግስት ያስቀመጣቸው የክልከላ አቅጣጫዎች እየተተገበሩ ባለመሆኑ እንዳሰጋቸው በደሴና ሀይቅ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
በሀይቅ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ሪ አቶ አደም ሹምዬ በሽታውን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ቢሆንም በአካባቢው አመራሮች ጨምሮ ብዛት ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ ሲሰበሰቡ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ይመር አራጋው በበኩላቸው የምሽት መዝናኛዎችና የተጨናነቀ የታክሲ እንቅስቃሴ መንግስት ቢከለክልም በአካባቢያቸው አሁንም በተለመደው ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንዳሉት ቫረሱን ለመከላከል በየደረጃው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል።
በተለያዩ ወረዳዎች የተጀመሩ ስብሰባዎችም እንዲቋረጡ መደረጉን ጠቁመው ከልክ በላይ የሚጭኑ ታክሲዎችንና የምሽት መዝናኛዎችን የተቋቋመው ግብረ ኃይል እንዲቆጣጠር አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡