በድሬዳዋ፣ ጌዲኦና ነቀምቴ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ፣ ጌዲኦና ነቀምቴ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ
ድሬደዋ/ ዲላ/ ነቀምቴ (ኢዜአ) መጋቢት 15/2012፡- በድሬደዋ ፣ ጌዴኦ ዞንና ነቀምቴ ከተማ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ።
፣መነበቨቸ
የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስን ተገን በማድረግ በሸቀጦችና ንጽህና መጠበቂያዎች ላይ ዋጋ በሚጨምሩ የንግድ ተቋማት ላይ የተቀናጀ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል፡፡
በሩዝ ተራና በቀፊራ የገበያ ስፍራዎች ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ 47 የእህል፣መሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጥ መሸጫ ሱቆችና መጋዘኖች እንዲታሸጉ ተደርጓል።
ከ20 በላይ ለሚሆኑት ተቋማት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
"በተጓዳኝም በዚህ ወሳኝና አንገብጋቢ ጊዜ ህብረተሰባቸው በታላቅ ታማኝነትና ቅንነት እያገለገሉ የሚገኙትን የንግዱን ማህበረሰብ የማበረታታትና የማጠናከር ሥራ ይሰራል" ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ግብአትና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲስተር ሰሪዶ ዑመር በበኩላቸው የሚስተዋለውን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ታያቸው በበኩላቸው በአካባቢው ተጠጋግቶ መመገብና በጋራ የመንቀሳቀስ ባህል ለጊዜው በመግታት ቫይረሱን ለመከላከል ሁሉም የግል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
ትልልቅ የጫት መቀንጠሻ አዳራሾች፣ መቃሚያዎችና መሸጫዎች ለቫይረሱ መተላለፍ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥሩ ነዋሪው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት " ያለው ደግሞ ወጣት ዘመድሁን በቀለ ነው።
በሌላ በኩል የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ጋሹ በዞኑ ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብረኃይሉ እስካሁን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 39 ወፍጮ ቤቶች፣ ሽንኩርት መሸጫ መደብሮች፣ የሽቀጣሸቀጥ ሱቆችና መድሃኒት ቤቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል።
ሌሎች 56 የሚሆኑ የንግድ ሱቆች ደግሞ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ህብረተሰቡ ሲገበያይ እንዳይጭበረበር ለማስቻል በሁሉም የንግድ ሱቆችና መደብሮች የዋጋ ተመን ዝርዝር እዲንዲለጠፉ መደረጉንም አቶ ወርቅነህ አስረድተዋል።
ግብረኃይሉ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የሚደበቁ ምርቶችን ለማጋለጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ በመሆኑ የአቅርበት እጥረት እንዳይከሰት አግዟል።
ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሪት ካሴች ደንበል በሰጡት አስተያየት በጤፍና ሽንኩርት ላይ በኪሎ የ20 ብር ጭማሪ መደረጉንና ነጭ ሽንኩርትን ግን በገበያ ላይ ማግኝት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
መንግስት የሸማቹን መብት ለማስከበር በየደረጃው የጀመረውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ክፍሌ ሳሊ በተለይ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ አልኮል በሚደብቁት ላይ ፈጣን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ አምስት ነዋሪ አቶ አለባቸው ተሾመ በከተማ ነጋዴው ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
የጤፍ ዋጋ በአንድ ጊዜ ከ3ሺህ 400 ብር ተነስቶ 4ሺህ ብር መግባቱን ጠቅሰው ይህም በከተማዋ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅና የሚረብሽ በመሆኑ አስተዳደሩ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
የቀበሌ አራት ነዋሪና ጡረተኛ የሆኑት አቶ ከበደ ዱፌራ በበኩላቸው የአንድ ኩንታል የጤፍ ዋጋ በአንድ ጊዜ የ500 ብር ጭማሪ ማሳየቱ የፈጠረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመው የከተማ አስተዳደሩ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
መጋቢት 12/2012 አቶ ኃይሉ ማሞ የተባለ ግለሰብ በአይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የንግድ ፍቃድ ሳይኖረው በከተማው እየተዘዋወረ አንድ ኩንታል ጤፍ በ3ሺህ 650 ብር ሲሸጥ በህዝብ ጥቂማ ተደርሶበት መያዙን የነቀምቴ ከተማ ወረዳ አንድ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሣጅን ነጋ በቀለ ተናግረዋል።
የከተማው አስተዳደር ንግድ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከኮሮን ጋር በተያያዘ ሕዝቡን በማደናገር አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 7 የእህል መጋዘኖች መታሸጋቸውን ቤት አስታውቀዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የንግድ ድርጅቶች የኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ የስራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ ትግሥት በቃና እንዳሉትመጋዘኖቹ የታሸጉት የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ እስከ 3ሺህ 500 ብር የነበረውን እስከ 500 ብር ጭማሪ አድረገው ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው።