ቀጥታ፡

ለይቶ ማቆያዎች ለሕብረተሰቡ ስጋት የሚፈጥሩ ሳይሆኑ ደሕንነቱን የሚያስጠብቁ ናቸው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ለተገመቱ ሰዎች የተዘጋጁ ለይቶ ማቆያዎች ለሕብረተሰቡ ስጋት የሚፈጥሩ ሳይሆኑ ደሕንነቱን የሚያስጠብቁ መሆናቸው ተገለጸ። 
ይህን የገለጸው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው።

የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ የማሕበረሰብ ንቅናቄ ባለሙያ አቶ መላኩ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በግንዛቤ ማነስ ሳቢያ ለይቶ ማቆያ ስፍራዎችን በስጋት የማየት ሁኔታ ተስተውሏል።

ለይቶ ማቆያ ቦታዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተገመቱ ሰዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅና ከተገኘባቸውም በቅርበት የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ቫይረሱ ከተስፋፋባቸው አገራት የሚመጡ ወይም ምልክት የታየባቸው ሰዎች በለይቶ ማቆያዎቹ እንዲቆዩ የሚደረገው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወዲያውኑ ምልክት ስለማያሳዩ እንደሆነም ገልጸዋል።

"ለይቶ ማቆያ በዚያ ያለ ሰው የባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እንዲያገኝ የሚያስችል ነው" ያሉት አቶ መላኩ ሕብረተሰቡም ይህንኑ ሊገነዘበው እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከተለያዩ አገራት መጥተው ኃላፊነት ተሰምቷቸው ሲመረመሩ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑበት ሁኔታ እንደነበረ ጠቁመው፣ አሁን የሚመጡትም ወደ ማቆያዎች እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።

"ይህም በሽታው በአገሪቱ እንዳይስፋፋና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል" ብለዋል።

በሌላ በኩል በሽታው በአገሪቷ መከሰቱ እየታወቀ አንዳንድ ሰዎች ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ የጠቆሙት አቶ መላኩ ይህ ለከፋ ጉዳት ስለሚዳርግ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ300 ሺህ መብለጡን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞችና ሠራተኞች የኮረናቫይረስ ያለበትን ደረጃና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም