ቀጥታ፡

የቡታ ጅራ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ

ሀዋሳ ሰኔ 23/2010 በጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላመጡት ለውጥ ድጋፋቸውን ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ ገለጹ፡፡ የከተማው ወጣቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተልዕኮ እንዲፈጸም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪ ወጣት ሸሚሹ አማን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ  ራዕይና እቅዳቸው መሳካት ከጎናቸው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡ " ሌብነትንና ዘረኝነትን እንድንታገል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሰጡንን ኃላፊነትና አደራ እንወጣለን "ብለዋል፡፡ የሰልፉ ዋና ዓላማ ዶክተር አብይ አህመድ ላመጧቸው ለውጦች እውቅና፣ ለመስጠትና ከጎናቸው በመሆን የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ከረጅም ዓመታት ኋላ ሀገሪቱ የፍቅር ፣የይቅርታና የእርቅ ምልክት ሆናለች  ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የሰልፉ ተሳታፊ አቶ አያሌው ታደሰ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያመጡ ያለው ለውጥ እንደወደዱላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላኛ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ከይራ የሀገሪቱን አንድነት ለመመለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍና ከጎኑ መቆማቸውን ለማሳየት በሰልፉ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ "ለሴቶችና እናቶች ከፖለቲካ ጥቅም ሳይሆን ለክብራቸውና እኩልነት መከበር ያሳዩት ፍቅር እንድወዳቸው አድርጎኛል" ብለዋል፡፡ " ላለፉት ሶስት ወራት ያጣናውን ሠላም መልሰን ያገኘኘው ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስለሆነ ለዘለቄታውመ  አብረን ከጎኑ እንሆናለን" ያለችው ደግሞ  ወጣት ሳራ አህመድ ናት፡፡ ሰልፈኞቹ ሰኔ 16 በአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት  አውግዘዋል፡፡ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቶፍቅ ሞሳ"  የእንደመር አዲስ አስተሳሰብ ከአንድ መቶ ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ህዝቦችን በፍቅርና በይቅርታ አዋህዷል" ብለዋል፡፡ የሚገጥሙ ችግሮች በውይይት በመፍታት የተጀመረውን ለውጥ በህብረት መስቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ለውጥን እንደግፋለን፣ ዴሞክራሲን እናበረታለን ፣ ከትንሽ አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ትልቅ አስተሳሰብ እንሻገራለን ፣ ቋንቋችን ቢለያይም ደማችን አንድ ነው ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጀን መደመር ብቻ ነው የሚሉ በሰልፉ ላይ ተሳታፊዎቹ ካሰሟቸው መፈክሮች ይገኙበታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም