ቀጥታ፡

ምዕመኑ በኮሮና ስጋት የራሱንም ሆነ የውጭ ዜጎችን ባለማግለል ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን እንዲያሳይ ቤተክርስቲያን ጠየቀች

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) ምዕመናን ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎችን ባለማግለል ኢትዮጵያዊ ጨዋነታቸውን እንዲያሳዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠየቀች ።

ቤተክርስቲያኗ በመላው አለም እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የእምነቱ ተከታዮች ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥታለች።

በዚህም ቋሚ ሲኖዶሱ የበሽታውን አስከፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት 13 መመሪያዎችን ለቤተክርስቲያን አገልጋዮችና ለዕምነቱ ተከታዮች አስተላልፏል።

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ አቡነ ማትያስ የዕምነቱ ተከታዩች በሰሞነ ህማማት እንደሚያደርጉት የእርስ በእርስ መሳሳምንና መጨባበጥን በማስቀረት ሌሎች የሰላምታ መለዋወጫ መንገዶችን በመከተል ራሳቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁ መክረዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ስርአተ ቅዳሴ በቤተ መቅደስ በካህናት ብቻ እንዲከናወንና ሌሎች አገልጋዮች ተራርቀው በመቆም እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

ከስርአተ ቅዳሴ በተጨማሪ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለስርአቱ በሚያስፈልገው የሰው ቁጥር ብቻና ውስን ሊቃውንት በተራ እንዲፈጸሙ መወሰኑን ገልጸዋል።

ምዕመናን ለቫይረሱ አጋላጭ ከሆኑ ተግባራት ራሳቸውን በመቆጠብ በቫይረሱ የተያዙትን፤ ያገገሙትንና የውጭ አገር ዜጎችን በክርስቲያናዊ ፍቅርና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንዲንከባከቡ መክረዋል።

ምዕመኑ በደስታ፣ በሃዘን፣ በስርአተ ቀብር አፈጻጸምና ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶችን በውስን የሰው ቁጥር እንዲያደርግም አሳስበዋል።

ወረርሽኙ ከአለም እስኪጠፋ ድረስ ካህናት በቤተ መቅደስ፣ በአውደ ምህረትና በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን እንዲያጥኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የተሰጡ መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንደሆኑና ቤተክርስቲያንን ከማይወክሉና ትክከል ካልሆኑ መረጃዎች በመቆጠብ የዕምነቱ አገልጋዮች ከቅዱስ ሲኖዱስ የሚሰጡ መመሪያዎችን እንዲያስፈጽሙ መወሰኑ ተገልጿል።

ለነዳያን እና ለተቸገሩ ዜጎች አስፈላጊውን ማህበራዊና ቁሳዊ እገዛ ምዕመኑ እንዲያደርግ አቡነ ማቲያስ  ጠይቀዋል።

የኮሮናን ወረርሽኝ ተከትሎ ቤተክርስቲያኗ ቀደም ሲል መንፈሳዊ ጉዞዎችንና ጉባኤዎችን እንዲሁም ምዕመናን በብዛት የሚሰበሰቡባቸው መርሃግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ መወሰኗ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም