በኮሮና የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ በሰብዓዊ ተግባራት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ በሰብዓዊ ተግባራት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ በሰብዓዊ ተግባራት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረበ።
ማህበሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም የሌላቸውን ዜጎች የጸረ ኮሮናቫይረስ ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፍ እርዳታ አሰባስቦ ዛሬ ለተጠቃሚዎች ሲያስተላልፍ በጎ ፈቃደኛ አባላትን ይዞ ተገኝቶ ነበር።
የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአደጋ ጊዜ ደራሹ ቀይ መስቀል በቅርቡ የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ከጤና ሚኒስቴር ግብረ ሃይል አባል በመሆን ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት ያለው ቀይ መስቀል በክልሎች ባሉት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም ላይ የቅድመ ጥንቃቄ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በተለያዩ ቋንቋዎች የማነቃቃት ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ማህበሩ ከ200 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደፈኛ አባላቱ በተጠቀቅ ላይ እንደሚገኙ፣ ሌሎች 5 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን ደግሞ እያሰለጠነ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ማህበራትና እህት ድርጅቶችም እስከ 20 ሚሊዮን ብር ገንዘብ የማሰባሰብ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በቫይረሱ መዛመት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስም 500 አምቡላንስ መኪኖች በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
እስካሁን ከ5 ሺህ በላይ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን መለገሱን፣ ለጥቁር አንበሳና ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር መሸሻ አስታውሰዋል።
ስራዎቹን በሁሉም ክልሎች ለማስፋት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ማህበረሰቡ የመረዳዳት እሴቱን ማጠናከር እንዳለበትና ማኅበሩን መደገፍ እንደሚገባው ገልጸዋል።
ከማኅበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከልም ወጣት መይት መልካሙና ፈቃዱ ተስፋዬም ወጣቶች ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከሚያሳልፉ የህሊና እረፍት በሚሰጡ የሰብዓዊ እርዳታዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
''ኢትዮጵያ የተደቀነባትን የኮሮናቫይረስ ስጋትም ጥንቃቄ በማድረግ ሃላፊነታችን በጋራ እንወጣ'' ሲሉ ጠይቀዋል።