ቀጥታ፡

የፈጠራ ባለሙያዎች የኮሮና ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የፈጠራ ሀሳቦችን አቀረቡ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 76 የፈጠራ ሀሳቦች በፈጠራ ባለሙያዎች መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ኢኖቬተርስ አሶሴሽን አስታወቀ።

ከ76ቱ ሀሳቦች 20ዎቹ መመረጣቸውንና ለሚመለከታቸው አካላት ከነገ ጀምሮ እንደሚቀርቡም ገልጿል።

አሶሴሽኑ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ የፈጠራ ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስን ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ የፈጠራ ሀሳቦች በፍጥነት እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጎ ነበር።

የአሶሴሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጃለታ ሙላቱ ጥሪው ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ 76 የፈጠራ ሀሳቦች በፕሮፖዛል መልክ መቅረባቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

''የፈጠራ ባለሙያዎቹ ያቀረቡት ሀሳብ አቅርቦትና አገልግሎት ላይ ያተኮሩ ናቸው'' ብለዋል።

የፈጠራ ሀሳቦቹ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አጠቃቀምና አወጋገድ፣ የታክሲ ወረፋ አጠባበቅና ርቀት መጠበቂያ ስርዓቶችና ተማሪዎች በክፍል ስለሚኖራቸው አቀማመጥ የሚያሳዩ ናቸው።

በአገልግሎት መስክ የቀረቡት የፈጠራ ሀሳቦች ንክኪ መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የፈጠራ ሀሳቦቹን ለመገምገም የተቋቋመው ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ 20 የፈጠራ ሀሳቦችን መለየቱን አስታውቀዋል።

ሀሳቦቹ የተመረጡት ባላቸው ተደራሽነት፣ በአነስተኛ ወጪ ማግኘት መቻልና ቶሎ ወደ ተግባር መግባት  በሚሉ መስፈርቶች መሆኑን አመልክተዋል።

የተመረጡት የፈጠራ ሀሳቦች ከነገ ጀምሮ ለሚመለከታቸው አካላት የማድረስ ስራ እንደሚጀመርና ባለድርሻ አካላቱ አዋጪና ውጤታማ የሚሏቸውን ሲያሳውቁ ሀሳቦቹ ወደ ትግበራ እንደሚገቡ አቶ ጃለታ አስረድተዋል።

ከ76ቱ መካከል በተቀመጡት መስፈርቶች የተሻሉ ናቸው የሚባሉት ሀሳቦች እየተገመገሙ ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

አሶሴሽኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የፈጠራ ሐሳቦቹ በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገቡ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

''አቅርቦትና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ በነጻ የማድረስ እቅድ አለ'' ያሉት አቶ ጃለታ፤ በነጻ ለማቅረብ ግን የድርጅቶችና የባለሀብቶችን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሌሎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሰዎችም አሁንም ሀሳባቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚከናወኑ ስራዎችን በፈጠራ ስራዎች ማገዛቸው ለህብረተሰቡ መፍትሔ ለማምጣት የሚጠበቅባቸው ሃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህም አንጻር ሁሉም የፈጠራ ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም አቶ ጃለታ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም