ህብረተሰቡ በቦንድ ግዥ ሳምንት መርሀ-ግብር ተሳትፎ አንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) ህዝቡ በቦንድ ግዥ ሳምንት መርሀ-ግብር አገራዊ ተሳትፎውን እንዲያደርግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የቦንድ ሽያጩን የሚያከናውነው ንግድ ባንክ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ዜጎች ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነም ገልጿል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 9ኛ አመት በማስመልከት የሚካሄደው የቦንድ ሳምንት ነገ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።

የዘንድሮ የቦንድ ሳምንት "ጤናችን ይጠበቃል፤ ግድባችን ይጠናቀቃል" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

በዚህም የቦንድ ሳምንት እስከ 500 ሚሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ ለማከናወን መታቀዱ ተገልጿል።

በዚህም ህዝቡ ከወቅቱ የጤና ችግር እራሱን እየጠበቀ ለግድቡ ግንባታ አሻራውን እንዲያሳርፍ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ህብረተሰቡ በቦንድ ሳምንቱ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አማካሪ ወይዘሮ አልማዝ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ''በቦንድ ሽያጭ ሳምንቱ የቦንድ ህትመት እጥረት እንዳይኖር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል'' ብለዋል።

በዚህም በቂ የቦንድ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ባንኩ ዝግጅቶቹን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን የቦንድ ሳምንቱን ለማከናወን በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በቦንድ ሽያጭ ሳምንቱም ከወቅቱ የኮሮናቫይረስ የጤና ስጋት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡን እጅ ከማስታጠብ ጀምሮ ለማስተናገድና በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የበኩሉን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ቦንድ በስጦታ ለሚያበረክቱ 1000291929609 እንዲሁም የቦንድ ግዢ ለሚፈጽሙ 1000291927738 የባንክ ሂሳብ ቁጥር መክፈቱ ተገልጿል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከኅብረተሰቡ 13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀምም ከ71 በመቶ በላይ መድረሱም ከማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም