ቀጥታ፡

በኮሮናቫይረስ ሥጋት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘት ተከለከለ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) መከሰትን ተከትሎ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘት መከልከሉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚንቀሳቀስ ከኢንቨስተሮች፣ ከሰራተኛ ማህበርና ከሰራተኛው የተውጣጣ  ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሚ እንዳሉት፤ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል አስቀድሞ ከተሰሩ ስራዎች መካከል ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመጎብኘት የሚመጣውን በርካታ የሰው ሃይል ማስቆም ነው።

በዚህም ሁሉንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የቫይረሱ ስጋት እስኪቀንስ ዝግ መደረጉን ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ዜጋ ወደ ኢንዱስትሪው ሲመጣ ለሁለት ሳምንታት በፓርኩ ባሉት የእንግዳ ማረፊያዎች ውስጥ በለይቶ ማቆያ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ተመርምረው ከጤና ሚኒስቴር ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ወረቀት እንዲያመጡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በፓርኮቹ ከ73 ሺህ በላይ የሰው ሃይል እንዳለ የሚናገሩት ስራ አስፈጻሚዋ፤ ''በስራቸው ባህሪ የተነሳ ለቫይረሱ ተጋላጭ የመሆን ዕድል አላቸው'' ነው ያሉት።

እነዚህን ዜጎች ለመታደግ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ጋር በመተባበር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ሰራተኞችም ከተለያዩ አካባቢዎች ስለሚመጡ፣ የትራንስፖርት ተጠቃሚ በመሆናቸውና የስራቸው ባህሪ በጣም ተጠጋግተው እንዲሰሩ ስለሚያደርጋቸው የፊት መሸፈኛና ጓንት እንዲያገኙ ተደርጓል።

ወጥተው ከህብረተሰቡ ጋር ስለሚገናኙ እራሳቸውን ከንክኪ ነጻ እንዲያደርጉና የግል ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጣቸው መሆኑን ወይዘሪት ሌሊሴ ተናግረዋል።

የሙቀት መለኪያ መሳሪያ ወደ ኢንዲስትሪ ፓርኮቹ ለመላክ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከመከሰቱ አስቀድሞ  በርካታ ተግባራትን በማከናወኑ ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና እንዳይደናገጡ ማገዙን አንስተዋል።

በፓርኮቹ ደረጃውን የጠበቀ የአፍ መሸፈኛ ማስኮችን ለማምረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም