የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በሰቆጣ እና ወልዲያ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በሰቆጣ እና ወልዲያ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ
ሰቆጣ/ወልዲያ ሰኔ 23/2010 የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍና አዲስ አበባ ላይ የተካሄደውን የቦንብ ጥቃት በማውገዝ ዛሬ በሰቆጣ እና በወልዲያ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች ተካሄዱ። በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ የተካሄደው ሰልፍ አስተባባሪ አቶ አስራት ታደሰ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና አዲሱ አመራር እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን ለማሳካት አንድነት ወሳኝ ነው። በተለይም ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በእርቅና በሰላም ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ለፍሬ እንዲበቃ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ያለስጋት ተንቀሳቅሶ የመኖር መብቱን የሚጥሱ አካሄዶች ሊወገዙ እንደሚገባቸውም አስተባባሪው አመልክተዋል። “ዶክተር ዐቢይ ለለውጥ የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን”፤ “ከጎንህ ነን”፣ “ጊዜው የመደመር ነው” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮችን የያዙ የከተማውና አካባቢው ወጣቶች፣ ሴቶችና ፣ ነጋዴዎችና ሌሎችም የህብረተስብ ክፍሎች በሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል። በተመሳሳይ “ጊዜው የመደመር ነው”፣ “የብሔረሰቦች ልዩነት ውበት እንጂ መለያ አይሆንም”፣ “የኃይማኖት መለያየት ለጠላት መሳሪያ መሆን የለበትም” የሚሉ መፈክሮችን ያነገቡ ሰልፈኞች በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ሼህ አላሙዲን ስታዲየም ድጋፍና አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል ወጣት ሽመልስ ወርቁ ባሰማው ንግግር ወጣቱ ትውልድ ሰላምና አንድነት የናፈቀው መሆኑን ገልጦ የወልዲያ ወጣት ይህን ሰላም ለማምጣት መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግሯል፡፡ "አሁን የተገኘው ነፃነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት እንዲመጣ የወልድያና የአካባበው ህዝብ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፤ አሁንም የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ በትጋት እንሰራለን "ብሏል። ከሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የመጡት መምህር አክሊለ ብርሃን ተመስገንም የሰው ልጅ ምንጩ አንድ በመሆኑ ከልዩነት ይልቅ አንድነቱ የባሕርይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰማው ታከለ የተባሉ የሰልፉ ታዳሚ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ ምክንያት እየተሰሩ እየተፈቱ ሲሰቃዩ መቆየታቸውን አስታውሰው "የአሁኑ ወቅቱ የ27 ዓመታት ጨለማ የተገፈፈበት ጊዜ ነው" ብለዋል፡፡ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወልደ ትንሳኤ መኮንን ለሰልፈኞቹ ባሰሙት የመዝጊያ ንግግር በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የቦንብ ጥቃት የፈጸሙትን አውግዘው ወጣቱ በራሱ ተነሳሽነት ለውጡን በመደገፉ አመስግነዋል፡፡ የድጋፍና የምስጋና ሰልፉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በጋራ በመዘመር በሰላም ተጠናቋል።