በአዲስ አበባ 37 መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ታሸጉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ 37 መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ታሸጉ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ከኮሮናቫይረስ መከላከያዎች አቅርቦት ጋር በተያያዘ ጥፋት የፈጸሙ 37 መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች መታሸጋቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጉዳዩን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው እንደገለጹት፤ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ 940 የመድሃኒት መደብሮች መካከል በ725ቱ ላይ ቁጥጥር ተደርጓል።
በተደረገው ቁጥጥር የተጋነነ ዋጋ ያቀረቡ፣ ምንጩ ያልታወቀ ምርት የሸጡና ምርቱ እያላቸው 'የለም' ሲሉ በነበሩ 37 የመድሃኒት መደብሮች ላይ የማሸግ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ከነዚህ በተጨማሪ 24 የመድሃኒት መደብሮች በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን ጠቁመዋል።
ሁለት የሳሙናና የዲተርጀንት አቅራቢነት ፈቃድ ያላቸው ግለሰቦች 'የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እና የእጅ ሳሙና እናመርታለን' በሚል ሲያታልሉ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የተጀመረው የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስገነዘቡት አቶ ደብረወርቅ፤ ምርቶቹን ተደራሽ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው ከመድሃኒት ቤቶችና መደብሮች በተጨማሪ በአስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ ቁጥጥር መደረጉን ገልጸዋል።
''አንዳንድ የመድሐኒት አስመጪና አከፋፋዮች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶችን ለማግኘት ሌላ መድሐኒት መውሰድ አለባችሁ በማለት ሰዎችን እያስገደዱ መሆኑ ተደርሶበታል'' ብለዋል።
ባለስልጣኑ በክልል ባሉት ስድስት ቅርንጫፎች የሚመጡለትን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ ክትልልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች አቅርቦትና ቁጥጥር ላይ ግብረሃይሎች ተቋቁመው እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከስኳር ኮርፖሬሽን የአልኮል አቅርቦት እንዲያገኙ መደረጉንና የሚጠጣ አልኮል የሚያምርቱ ፋብሪካዎች የንጽህና መጠበቂያ አልኮል እንደሚያመርቱ እየተደረገ እንደሆነ ነው ወይዘሪት ሄራን ያስረዱት።
ከአገር ውስጥ አምራቾችና አከፋፋዮች ጋር ውይይት በማድረግ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ለይተው ወደ ማምረትና ወደ ማቅረብ መግባታቸውን አመልክተዋል።
ለስምንት የሚሆኑ ድርጅቶች ባለስልጣኑ የሳኒታይዘር ማምረት ፈቃድ መስጠቱንና የአፍ መሸፈኛ ማስክና ጓንት እናመርታለን ለሚሉ ድርጅቶችም ፈቃድ እየተሰጠ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ድርጅቶቹ አቅማቸው ከተጠናከረና በፍጥነት የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ካመረቱ ግብአቶቹን ማዳረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
አዲ"አሁን ባለው ደረጃ ለሁሉም ተደራሽ ተደርጓል ባይባልም ግን ዝግጅቱ በዛ ደረጃ ስለሆነ በቀጣይ ያለ ችግር ግብዓቱ ይቀርባል ብለን እናስባለን" ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ አክለዋል።